5. የተስፋው ልጅ

አብራምና ሦራ ከነዓን ከደረሱ ከዐሥር ዓመታት በኋላ እንኳ ልጅ አልነበራቸውም። ስለዚህም የአብራም ሚስት ሦራ እንዲህ አለችው ‹‹እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ ስለከለከለኝና እኔም ከእንግዲህ እንዳልወልድ ስላረጀሁ አገልጋዬ አጋር ይህችትልህ፤ አግባትና ለኔ ልጅ ትውለድለኝ›› አለችው።

ስለዚህ አብራም አጋርን አገባት። አጋርም ወንድ ልጅ ወለደች። አብራምም ‹‹እስማኤል›› ሲል ስም አወጣለት። ይሁን እንጂ ሦራ በአጋር ቀናችባት። እስማኤል ዐሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነው እግዚአብሔር ለአብራም እንደገና ተናገረው።

እግዚአብሔርም አብራምን ‹‹እኔ ኤልሻዳይ አምላክ ነኝ፤ ካንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ›› አለው። አብራምም በግምባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እግዚአብሔርም አብራምን አለው ‹‹አንተ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። የከነዓንን ምድር ለአንተና ለዘርህ ርስት አድርጌ እሰጥሃለው። እኔም ለዘላለም አምላካቸው እሆናለሁ። አንተም በቤተ ሰብህ የሚገኘውን ወንድ ሁሉ መግረዝ አለብህ›› አለው።

እግዚአብሔርም ‹‹ሚስትህ ሦራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች። እርሱም የተስፋው ልጅ ይሆናል። ስሙን ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ። ኪዳኔንም ከእርሱ ጋር አደርጋለሁ። እርሱም ታላቅ ሕዝብ ይሆናል። እስማኤልንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃል ኪዳኔ ከይስሐቅ ጋር ይሆናል›› አለው። እግዚአብሔርም የአብራምን ስም ‹‹አብርሃም›› ሲል ለወጠለት፤ ትርጓሜውም ‹‹የብዙዎች አባት›› ማለት ነው። እግዚአብሔር የሦራንም ስም ‹‹ሣራ›› ሲል ለወጠላት፤ ትርጓሜውም ‹‹ልዕልት›› ማለት ነው።

በዚያኑ ዕለት አብርሃም በቤተ ሰቡ የሚኙትን ወንዶች ሁሉ ገረዘ። ከዓመት በኋላ አብርሃም 100 ዓመት ሲሆነውና ሣራ 90 ዓመት በሆናት ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። እግዚአብሔርም እንዳላቸው ‹‹ይስሐቅ›› ሲሉ ስም አወጡለት።

ይስሐቅ ወጣት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር የአብርሃምን እምነት እንዲህ ሲል ፈተነው፤ ‹‹አንድዬ ልጅህን ይስሐቅን ውሰድና ለኔ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብልኝ›› አለው። እንደ ገና አብርሃም እግዚአብሔርን ታዘዘና ልጁን ሊሠዋው ተዘጋጀ።

አብርሃምና ይስሐቅ መሥዋዕት ወደሚደረግበት ስፍራ በመጓዝ ላይ ሳሉ ይስሐቅ አባቱን ‹‹አባቴ ሆይ ለመሥዋዕት ማቅረቢያ እንጨቱ ይኸውና፤ በጉ ግን የታለ?›› ሲል ጠየቀ። አብርሃምም ‹‹ልጄ ሆይ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ሲል መለሰለት።

ወደ መሥዋዕት ማቅረቢያ ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን አስሮ በመሠዊያው ላይ አጋደመው። አብርሃምም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን ባነሣ ጊዜ፤ እግዚአብሔር “ተው፤ በልጁ ላይ ምንም ጉዳት አታድርስበት። አንድዬ ልጅህን ሳትሳሳ ለእኔ በመስጠትህ እኔን እንደምትፈራኝ አሁን አውቄአለሁ” አለው።

በአቅራቢያው አብርሃም በቊጥቋጦ ውስጥ የታሰረ በግ አየ። እግዚአብሔር በይስሐቅ ፋንታ ለመሥዋዕት የሚሆን በግ አዘጋጅቶ ነበር። አብርሃምም በደስታ በጉን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ።

እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፣ ‹‹አንድያ ልጅህን እንኳ ሳይቀር ያለህን ሁሉ ልትሰጠኝ ፍቃደኛ ነህና ልባርክህ ቃል እገባለሁ። ዘሮችህ ከሰማይ ክዋክብት ይልቅ ይበዛሉ፤ እኔን ስለ ታዘዝከኝ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 16-22፡፡