46. ጳውሎስ ክርስቲያን ሆነ

ሳውል እስጢፋኖስ ሲገደል የገዳዮችን ልብስ ይጠብቅ የነበረ ወጣት ነው። እርሱ በኢየሱስ የማያምን ነበር፣ ስለዚህም አማኞችን ያሳድድ ነበር። ወንዶችንና ሴቶችን እየያዘ ወደ እስር ቤት ለመጨመር በኢየሩሳሌም ከቤት ወደ ቤት ይሄድ ነበር። ሊቀ ካህናቱ በዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ይይዝና ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ ወደ ደማስቆ ከተማ እንዲሄድ ለሳውል ፈቃድ ሰጡት።

ሳውል ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ እያለ፣ ከሰማይ ብሩህ ብርሃን በዙሪያው ሁሉ አበራ፣ እርሱም መሬት ላይ ወደቀ። ከዚያም፣ ‹‹ሳውል! ሳውል! ስለ ምን ታሳድደኛለህ?›› የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውል፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ?›› ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ ‹‹የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ›› ብሎ መለሰለት።

ሳውልም ከወደቀበት በተነሣ ጊዜ፣ ማየት ተሳነው። ወዳጆቹ ወደ ደማስቆ እየመሩ ወሰዱት። ሳውል ለሦስት ቀናት ምንም አልበላም ወይም አልጠጣም።

በደማስቆ ሐናንያ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። እግዚአብሔር ለሐናንያ፣ ‹‹ሳውል ወዳለበት ቤት ሂድ። እንደ ገና ያይ ዘንድ እጅህን ጫንበት›› አለው። ሐናንያ ግን፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው አማኞችን እንዴት እንዳሳደደ ሰምቼአለሁ›› አለ። እግዚአብሔር፣ ‹‹ሂድ! ለአይሁዶችና ለአሕዛብ ስሜን እንዲያውጅ መርጬዋለሁ። ስለ ስሜ ብዙ መከራ ይቀበላል›› አለው።

ስለዚህ ሐናንያ ወደ ሳውል ሄደ። እጆቹን ጫነበት፣ እንዲህም አለ፣ ‹‹ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የታየህ ኢየሱስ፣ እንደ ገና ታይና በመንፈስ ቅዱስ ትሞላ ዘንድ ወዳንተ ላከኝ።›› ሳውል ወዲያውኑ ማየት ቻለ፣ ሐናንያም አጠመቀው። ከዚያ በኋላ ሳውል ምግብ በላ፣ በረታም።

ሳውል ወዲያውኑ፣ ‹‹ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው!›› በማለት በደማስቆ ለነበሩ አይሁድ መስበክ ጀመረ። አይሁዶች አማኞችን ለማጥፋት የሞከረው ሰው አሁን ደግሞ በኢየሱስ በማመኑ ተደነቁ! ሳውል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለአይሁዶች አረጋገጠላቸው።

ከብዙ ቀናት በኋላ አይሁዶች ሳውልን ለመግደል ዐቀዱ። ይገድሉት ዘንድ በከተማይቱ በሮች የሚጠባበቁትን ሰዎች አቆሙ። ነገር ግን ሳውል ስለ ዕቅዱ ሰማ፣ ወዳጆቹም እንዲያመልጥ ረዱት። አንድ ሌሊት በቅርጫት አድርገው በከተማዪቱ ቅጥር አወረዱት። ሳውል ከደማስቆ ካመለጠ በኋላ ስለ ኢየሱሰ መስበኩን ቀጠለ።

ሳውል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፣ እነርሱ ግን ፈሩት። በዚያን ጊዜ በርናባስ የተባለ አማኝ ሳውልን ወደ ሐዋርያቱ ወሰደውና ሳውል በደማስቆ እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሳውልን ተቀበሉት።

በኢየሩሳሌም ከነበረው ስደት የሸሹ አንዳንድ አማኞች ወደ አንጾኪያ ድረስ ርቀው ሄዱና ስለ ኢየሱስ ሰበኩ፡፡ በአንጾኪያ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች አይሁዶች አልነበሩም፣ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙዎቻቸው በኢየሱስ አመኑ፡፡ በርናባስና ሳውል እነዚህን ዐዳዲስ አማኞች በተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ሊያስተምሯቸውና ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠናክሩ ወደዚያ ሄዱ፡፡ በኢየሱስ ያመኑት ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ‹‹ክርስቲያኖች›› ተባሉ፡፡

አንድ ቀን በአንጾኪያ የነበሩ ክርስቲያኖች እየጾሙና እየጸለዩ እያሉ መንፈስ ቅዱስ፣ ‹‹ለጠራኋቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ›› አላቸው። ስለዚህ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለበርናባስና ለሳውል ጸለዩላቸው፣ እጆቻቸውንም ጫኑባቸው። ከዚያም በሌሎች ብዙ ቦታዎች ስለ ኢየሱስ የምሥራች እንዲሰብኩ ላኩአቸው። በርባናስና ሳውል ከተለያዩ የሕዝብ ወገኖች የሆኑ ሰዎችን አስተማሩ፣ ብዙ ሰዎችም በኢየሱስ አመኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 8፡3፤ 9፡1-31፤ 11፡19-26፤ 13፡1-3።