42. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለሰ

ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ በአቅራቢያው ወዳለች ከተማ እየሄዱ ነበር። ሲጓዙም፣ በኢየሱስ ላይ ስለ ደረሰበት ነገር ሲነጋገሩ ነበር። እርሱ መሲሕ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገው ነበር፣ ነገር ግን እርሱ ተገደለ። አሁን ሴቶቹ እንደ ገና ሕያው ሆኖአል አሉ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የቱን ማመን እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸው ነበር።

ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበና አብሮአቸው መጓዝ ጀመረ፣ እነርሱ ግን ዐላወቁትም ነበር። ስለ ምን ይነጋገሩ እንደ ነበረ ጠየቃቸው፣ እነርሱም ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ኢየሱስን በተመለከተ ስለ ሆኑት አስገራሚ ነገሮች ሁሉ ነገሩት። የሚነጋገሩት በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ከማያውቅ ከእንግዳ ሰው ጋር መስሏቸው ነበር።

ከዚያም ኢየሱስ፣ ስለ መሲሑ የእግዚአብሔር ቃል የተናገረውን አብራራላቸው። መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል፣ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ነቢያት የተናገሩትን አስታወሳቸው። ሁለቱ ሰዎች ሊያድሩባት ወዳሰቡአት ከተማ ሲደርሱ፣ ጊዜው መሽቶ ነበር።

ሁለቱ ሰዎች ከእነርሱ ጋር እንዲያድር ኢየሱስን ጋበዙት፣ እርሱም እሺ አላቸው። እራት ለመብላት በተዘጋጁ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ እግዚአብሔርን አመሰገነ፣ ከዚያም ቈረሰው። ወዲያውኑ ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እርሱ ከዓይናቸው ተሰወረ።

ሁለቱም ሰዎች፣ ‹‹ኢየሱስ ነው! የእግዚአብሔርን ቃል ሲያብራራልን ልባችን ሲቃጠልብን የነበረው ስለዚህ ነው!›› ተባባሉ፡፡ ወዲያውኑ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ በደረሱም ጊዜም ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹ኢየሱስ ሕያው ነው! ዐይተነዋል!›› ብለው ነገሩአቸው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ እየተነጋገሩ እያሉ፣ ኢየሱስ በድንገት በነበሩበት ክፍል በመካከላቸው ተገኘና፣ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን!›› አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ መሰላቸው፣ ኢየሱስ ግን፣ ‹‹ለምን ትፈራላችሁ፤ ትጠራጠራላችሁም? እጆቼንና እግሮቼን እዩ። መናፍስት እንደ እኔ አካል የላቸውም›› አላቸው። መንፈስ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚበላ ነገር እንዲሰጡት ጠየቃቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ሰጡት፣ እርሱም በላ።

ኢየሱስም፣ ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ ነግሬአችኋለሁ›› አለ። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲረዱ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። ‹‹መሲሑ መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ ከረጅም ዘመን በፊት ተጽፎአል›› አላቸው።

“ደግሞም የኃጢአታቸውን ይቅርታ ለማግኘት ሰዎች ሁሉ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ደቀ መዛሙርቴ እንደሚያውጁ በመጻሕፍት ተጽፎአል። እነርሱ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ይህን ያደርጋሉ፣ ከዚያም በሁሉም ስፍራ ወዳሉ የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ይሄዳሉ። እናንተ የእነዚህ ነገሮች ምስክሮች ናችሁ።” አላቸው።

በቀጣዮቹ አርባ ቀናት ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። አንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች በአንድ ጊዜ ታይቷቸው ነበር! እርሱ ሕያው መሆኑን በብዙ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋገጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱ፣ የሕዝብ ወገኖችን ሁሉ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው። እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።››

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ ከአርባ ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ ወርዶ ኃይልን እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ›› አላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ወጣ፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረችው፡፡ ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ሊገዛ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 28፡16-20፤ ማርቆስ 16፡12-20፤ ሉቃስ 24፡13-53፤ ዮሐንስ 20፡19-23፤ የሐዋርያት ሥራ 1፡1-11።