አማርኛ: Open Bible Stories
1. ፍጥረት

እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የፈጠረው እንደሚከተለው ነው፡፡እግዚአብሔር ዓለምንንና በውስጧ የሚገኙትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ፈጠረ፡፡ እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረ በኋላ ምድር ጨለማና ባዶ ነበረች፤ በውስጧ ምንም ነገር ገና አልተፈጠረም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ በውሆች ላይ ነበር፡፡

ከዚያም እግዚአብሔር ‹‹ብርሃን ይሁን›› አለ ፤ ብርሃንም ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አይቶ ‹‹ቀን›› ብሎ ጠራው፡፡ እግዚአብሔርም ቀኑን ከጨለማ ለይቶ ጨለማውን ሌሊት ብሎ ጠራው፡፡ እግዚአብሔርም በመጀመሪያው ቀን ብርሃንን ፈጠረ፡፡

በሁለተኛው የፍጥረት ቀን እግዚአብሔር ከምድር በላይ ያለውን ጠፈር በቃሉ ፈጠረ፡፡ በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ከጠፈር በለይ ያለውን ውሃ ከጠፈር በታች ካለው ውሃ የሚለይ ሰማይን ፈጠረ።

በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር በቃሉ ውሃውን ከየብሱ መሬት እንዲለይ አደረገ፡፡ እግዚአብሔርም የብሱን መሬት ‹‹ምድር›› ውሃውንም ‹‹ባሕር›› ብሎ ጠራው፡፡ እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ፡፡

ከዚያም እግዚአብሔር ምድር ሁሉንም ዓይነት ዛፎችንና ተክሎችን ታብቅል አለ፣ እንዲሁም ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ፡፡

በአራተኛው የፍጥረት ቀን እግዚአብሔር ፀሐይን፣ ጨረቃንና ክዋክብትን በቃሉ ፈጠረ፡፡ እግዚአብሔርም እነዚህ ለመሬት ብርሃን እንዲሰጡ ቀንና ሌሊትንም ወቅቶችንና ዓመታትንም እንዲለዩ አደረገ፡፡ እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ፡፡

በአምስተኛው ቀን እግዚአብሔር በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ወፎችን ሁሉ በቃሉ ፈጠረ፡፡ እግዚአብሔር ያ መልካም እንደ ሆነ አየ፤የተፈጠሩትንም ባረካቸው፡፡

በስድስተኛው ቀን፣ እግዚአብሔር ‹‹ምድር ሁሉንም ዓይነት እንስሳት ታውጣ›› አለ፡፡እነሱም ልክ እግዚአብሔር እንዳለውም ሆኑ፡፡ አንዳንዶቹ የቤት እንስሳት፣ አንዳንዶቹ በምድር የሚሳቡ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የዱር እንስሳት ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ፡፡

እግዚአብሔር ‹‹ሰዎችን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር እነርሱም በምድርና በእንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው›› አለ፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር ከምድር አፈር ወስዶ ሰው አድርጐ አበጀና የሕይወትን እስትንፋስ በአፍንጫው እፍ አለበት፡፡ የዚህም ሰው ስም አዳም ተባለ፡፡ እግዚአብሔር አዳም የሚኖርበትን የኤደን ገነት አበጀውና ስፍራውን እንዲያለማው እዚያ አስቀመጠው፡፡

በገነትም መካከል እግዚአብሔር ሁለት የተለዩ ዛፎችን ተከለ፤እነርሱም የሕይወት ዛፍና መልካምና ክፉን እንዲያውቁ የሚያስችል የእውቀት ዛፍ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርም አዳምን መልካምንና ክፉን መለየት ከሚያስችለው የእውቀት ዛፍ በቀር በገነት ውስጥ ካለው ከየትኛውም ዛፍ መብላት እንደሚችል ነገረው፡፡ ነገር ግን ክፉውንና መልካሙን እንዲያውቁ ከሚያስችለው ዛፍ ቢበላ እንደሚሞትም ነገረው፡፡

ከዚያም እግዚአብሔር ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም አለ፡፡ ከእንስሳቱ አንዳቸውም የአዳም ረዳት ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት። አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራትና ወደ አዳም አመጣት፡፡

አዳምም ባያት ጊዜ እንዲህ አለ፤ ‹‹ይህችስ እኔኑ ትመስላለች! ስለዚህ ከወንድ ተገኝታለችና ስሟ ሴት ትባል አለ፡፡” (በእብራይስጥ ከኢሽ ተገኝታለችና ስሟ ኢሻህ ትባል ይላል)፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፡፡

እግዚአብሔር ወንድና ሴትን በራሱ መልክ ፈጠረ፡፡ እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ አላቸውም ‹‹ብዙ ተባዙ፤ ልጆችና የልጅ ልጆችንም ውለዱ ምድርንም ሙሉአት፡፡›› እግዚአብሔርም የሠራው ነገር ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ እንደ ሆነ አየ፡፡ በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ አለው። ይህ ሁሉ በስድስት የፍጥረት ቀናት ሆኑ።

በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ፈጸመ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሲሠራው ከነበረው ሥራ ሁሉ አረፈ፤ ስለዚህ ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቀን ከሥራው ሥራ ሁሉ አርፏልና፡፡ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በውስጣቸውም የሚገኙትን ሁሉ የፈጠረው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 1-2፡፡
2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ

አዳምና ሚስቱ እግዚአብሔር በሠራላቸው ውብ የአትክልት ስፍራ ሲኖሩ በጣም ደስተኞች ነበሩ። ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ራቁታቸውን በመሆናቸው አይተፋፈሩም ነበረ፤ ምክንያቱም ኃጢአት በዓለም አልነበረም። እነርሱም በአትክልቱ ስፍራ እየተመላለሱ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገሩ ነበር።

ነገር ግን ተንኮለኛ እባብ በአትክልቱ ውስጥ ነበር። እባቡም ሴትየዋን ‹‹እግዚአብሔር በእርግጥ በአትክልቱ ውስጥ ካለው ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ አዞዋችኋልን?›› ብሎ ጠየቃት።

ሴቲቱም፣ ‹‹እግዚአብሔር ክፉንና መልካሙን ከሚያሳውቀው የእውቀት ዛፍ በስተቀር ከማንኛውም የዛፍ ፍሬ መብላት እንደምንችል ተናግሮናል። ነገር ግን ‹ያንን ዛፍ ፍሬ ብትበሉ ወይም ብትነኩት እንኳ ትሞታላችሁ› አለን።

እባቡም ለሴቲቱ መልሶ፣ “ይህ እውነት አይደለም፤ አትሞቱም። ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ወዲያውኑ ዓይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምንና ክፉን በማወቅ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው አትብሉት ያላችሁ›› አለ።

ሴቲቱም የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዓይንም የሚያስደስትና የሚያስጎመጅ እንደሆነ አየች። ጥበብንም ለማግኘት ስለጓጓች ከፍሬው ወስዳ በላች። ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏም ሰጠችው። እርሱም ከዛፉ ፍሬ በላ።

ወዲያውም የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ። ራቁታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ፤ ቅጠልም እንደ ልብስ ሰፍተው ራቁትነታቸውን ለመሸፈን ሞከሩ።

ከዚያም አዳምና ሚስቱ የእግዚአብሔር ድምፅ በአትክልቱ መካከል ሲመላለስ ሰምተው ሁለቱም ከእግዚአብሔር ፊት ተሸሸጉ። እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ ‹‹የት ነህ?›› አለው። አዳምም ‹‹በአትክልቱ ስፍራ ስትመላለስ ሰማሁ፤ ራቁቴን ስለ ሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም›› ብሎ መለሰ።

እግዚአብሔርም ‹‹ራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ከርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?›› አለው።አዳምም፣ ‹‹ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ›› አለው። እግዚአብሔርም ሴቲቱን ‹‹ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?›› አላት። እርሷም፣ ‹‹እባብ አሳሳተኝና በላሁ›› አለች።

እግዚአብሔር እባቡን እንዲህ አለው፤ ‹‹አንተ የተረገምህ ነህ፣ በደረትህ ትሳባለህ፤ አፈርም ትበላለህ፤ በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤የሴቷ ዘር እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።››

እግዚአብሔር ሴቲቱንም አላት ‹‹በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፣ ፍላጎትሽ ወደ ባልሽ ይሆናል እርሱም ይገዛሻል።››

እግዚአብሔርም አዳምን እንዲህ አለው። ‹‹የሚስትህን ቃል ሰምተህ አትብላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ ፍሬ በልተሃልና ምድር ካንተ የተነሣ የተረግመች ትሁን። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ከዚያም ትሞታለህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ።›› አዳምም ሚስቱን የሕያዋን ሁሉ እናት ስለሆነች ሔዋን ብሎ ጠራት፤ ትርጓሜውም ሕይወት ሰጪ ማለት ነው፤ እግዚአብሔርም ከእንስሳ ቆዳ አዘጋጅቶ አዳምንና ሔዋንን አለበሳቸው።

ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር መከልከል አለበት›› አለ። ስለዚህ አዳምንና ሔዋንን ከውቡ የአትክልት ስፍራ አስወጣቸው።ከዚያም ማንም የህይወት ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ እንዲጠብቁ ኃይለኞች መላእክትን በአትክልቱ ስፍራ መግቢያ ላይ አኖረ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ዘፍጥረት 3
3. የጥፋት ውሃ

ከረጅም ጊዜ በኋላ ብዙ ሕዝቦች በዓለም ይኖሩ ነበር። እነርሱም በጣም ክፉዎችና አመጸኞች ሆኑ። ክፋትም በጣም ስለበዛ እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ በከባድ የጥፋት ውሃ ለማጥፋት ወሰነ።

ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ። ኖኅ በክፉ ሰዎች መካከል የሚኖር ጻድቅ ሰው ነበር። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ሊያመጣ ስላቀደው የጥፋት ውሃ ለኖኅ ነገረው። ኖኅም ግዙፍ መርከብም እንዲሠራ እግዚአብሔር ነገረው።

የመርከቢቱም ርዝመት 140 ሜትር ወርዷ 23 ሜትር ከፍታዋ 13.5 ሜትር ይሁን አለው። ኖኅ የሚሠራት መርከብ ከእንጨት የተሠራች ሆና ባለ ሦስት ፎቅ፤ ብዙ ክፍሎች፤ ጣራና መስኮት ያሉአት ነበረች። መርከቢቱም ኖኅንና ቤተ ሰቡን፣ ሁሉንም ዓይነት የምድር ላይ እንስሳት ከጥፋት ውሃ እንድትጠብቅ ነገረው።

ኖኅም እግዚአብሔርን በመታዘዘ እግዚአብሔር እንደ ነገራው መርከቢቱን ሠራ። መርከቧ በጣም ትልቅ ስለነበረች ለመጨረስ ብዙ ዓመታት ፈጀ። ኖኅ ስለሚመጣው የጥፋት ውሃ ለሕዝቡ እያስጠነቀቀ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይነግራቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ አላመኑትም።

እግዚአብሔር ኖኅንና ቤተ ሰቡን በቂ ምግብ ለራሳቸውና ለእንስሳቱ እንዲያከማቹ አዘዘ። ሁሉም ነገር ዝግጁ በሆነ ጊዜ ለኖኅ፣ ለሚስቱ፣ ለሦስቱ ወንዶች ልጆቹና ለሚስቶቻቸው ወደ መርከቢቱ ለመግባት ጊዜው መድረሱን ነገረው። ስምንት ሰዎችም ወደ መርከቢቱ ገቡ።

እግዚአብሔር ከጥፋት ውሃው እንዲድኑ የሁሉንም ተባእትና እንስት እንስሳት ወፎችንም ጨምሮ ወደ ኖኅ ላከ። ለመሥዋዕት የሚያገለግሉ ሰባት ተባእትና ሰባት እንስት ከሁሉም ዓይነት እንስሳ ወደ ኖኅ መርከብ ላካቸው። ሁሉም ወደ መርከቡ እንደ ገቡ እግዚአብሔር ራሱ የመርከቡን በር ዘጋ።

ከዚያም ዝናቡ መዝነብ ጀመረ፣ ዘነበ፣ ዘነበ፣ ዘነበ ያለማቋረጥ ለ40 ቀንና ሌሊት ዘነበ፣ ከምድርም ምንጭ ይፈልቅ ነበር። በመላው ዓለም ያለው ሁሉም ነገር በውሃ ተሸፈነ፤ ረጃጅም ተራሮች እንኳ ሳይቀሩ በውሃ ተሸፈኑ።

በመርከቡ ከነበሩት ሰዎችና እንስሳት በቀር በምድር ይኖር የነበረ ነገር ሁሉ ሞተ፤ መርከቢቱም በውሃው ላይ ተንሳፍፋ በውስጧ የሚገኙትን ነፍሳት ሁሉ ከሞት አዳነች።

ዝናቡ መዝነቡን ካቆመ በኋላ መርከቢቱ ለአምስት ወራት ያህል በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። በዚህም ጊዜ ውሃው መቀነስ ጀመረ። ከዕለታት አንድ ቀን መርከቢቱ በተራራው አናት ላይ አረፈች፤ ይሁን እንጂ ዓለም አሁንም በውሃ ተሸፍና ነበር። ከሦስት ወራት በኋላ የተራሮች ጫፎች መታየት ጀመሩ።

ከአርባ ቀናት በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ ደርቆ እንደ ሆነ እንዲያይ ቁራ የተባለን ወፍ/አሞራ ላከ። ቁራው እዚህም እዚያም እየበረረ ደረቅ መሬት ቢፈልግም ሊያገኝ አልቻለም።

በኋላም ኖኅ ርግብ የተባለች ወፍ ላከ። ይሁን እንጂ የምታርፍበት መሬት ማግኘት ስላልቻለች ወደ ኖኅ ተመልሳ መጣች። ከሳምንት በኋላ ኖኅ እንደ ገና ርግቧን ላካት። እርሷም የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ተመለሰች። ውሃው ይቀንስ ስለ ነበር ተክሎችም ደግሞ መብቀል ጀመሩ።

ኖኅ ሌላ አንድ ሳምንት ጠብቆ ርግቢቷን ለሦስተኛ ጊዜ ሰደዳት፤ በዚህ ጊዜ የምታርፍበት ስፍራ ስላገኘች ተመልሳ አልመጣችም። ውሃው እየደረቀ ነበር።

ከሁለት ወራት በኋላ እግዚአብሔር ኖኅን “አንተ ቤተሰብህና እንስሳቱ በሙሉ ከመርከቧ ውጡ። ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆችን ወለዱ፤ ምድርንም ሞሉአት” አለ።

ስለዚህ ኖህና ቤተሰቡ ከመርከብ ወጡ ።ኖኅም ከመርከቢቱ ከወጣ በኋላ መሠዊያ ሠራና ከእያንዳንዱ እንስሳ ለመሥዋዕት ሊቀርቡ የሚችሉትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕትአቀረበ። እግዚአብሔርም በመሥዋዕቱ ተደሰተ፤ ኖኅንና ቤተ ሰቡን ባረካቸው።

እግዚአብሔርም ‹‹ሰዎች ስለሚያደርጉት ክፉ ነገር ዳግም በጥፋት ውሃ አይጠፉም። ምንም እንኳ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ክፉዎች ቢሆኑም ዓለምን ዳግመኛ በጥፋት ውሃ አላጠፋም›› አለ።

እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ምልክት ይሆን ዘንድ የመጀመሪያውን ቀስተ ደመና ሠራ። ሁልጊዜ ቀስተ ደመናው በሰማይ ላይ ይታያል። እግዚአብሔር በዚህ ቀስተ ደመና አማካይነት ለሕዝቡ የገባውን ኪዳን ያሳታውሳል፤የርሱ ሕዝብም እንዲሁ ያስታውሳል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 6-8
4. የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከአብርሃም ጋር

ከጥፋት ውሃው ከብዙ ዓመታት በኋላ ሕዝቦች በዓለም ላይ እንደገና በዙ። ሁሉም አንድ አይነት ቋንቋ ይናገሩ ነበር። እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ምድርን በመሙላት ፋንታ በአንድነት ተሰብስበው ከተማ ሠሩ።

እነርሱም በጣም ትምክህተኞችና እግዚአብሔር የተናገራቸውን ነገር የማይሰሙ ነበሩ። እንዲያውም ወደ ሰማይ ሊደርሱ ረጅም ሕንጻ መገንባት ጀመሩ። እግዚአብሔርም እነዚህ ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው ክፉ መሥራታቸውን ከቀጠሉ ከዚህም የከፋ ብዙ ኃጢአት ማድረግ እንደሚችሉ አየ።

ስለዚህም እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ወደ ብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች ደበላለቀና ሕዝቡን በዓለም ሁሉ በተናቸው። ሊሠሩት የጀመሩት ከተማ ስም ባቤል ይባላል። የስሙም ትርጓሜ የተደባለቀ ወይም ግራ የተጋባ ማለት ነው።

ከመቶ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር አብራም የተባለውን ሰው ተናገረው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው “አገርህንና ቤተ ሰብህን ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። በዚያም እባርክሃለሁ፣ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፣ የሚባርኩህን እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ሰዎች ሁሉ ባንተ ይባረካሉ።”

አብራምም እግዚአብሔርን ታዘዘ፤ ሚስቱን ሦራንና አገልጋዮቹን ሁሉና ንብረቱንም ሁሉ ይዞ እግዚአብሔር ወዳሳየው የከነዓን ምድር ሄደ።

አብራም ከነዓን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ‹‹በዙሪያህ ያለውን ሁሉ ተመልከት፤ይህን የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘሮችህ ውርስ አድርጌ እሰጣችኋለሁ›› አለው። አብራምም በምድሪቱ ተቀመጠ።

ከዕለታት አንድ ቀን አብራም መልከ ጼዴቅ የተባለውን የልዑል እግዚአብሔር ሊቀ ካህን ተገናኘው። መልከ ጻዴቅም አብራምን ባረከው፤ እንዲህም አለው ‹‹የሰማይና የምድር ጌታ ልዑል እግዚአብሔር አብራምን ይባርክ››። አብራምም ለመልከ ጼዴቅ ካለው ሁሉ አሥራት ሰጠው።

አብራምና ሦራ አሁንም ያለ ልጅ ብዙ ዓመታት ኖሩ። እግዚአብሔር ለአብራም እንደ ገና ተናገረውና ልጅ እንደሚወልድና ዘሮቹ እንደ ሰማይ ክዋክብት እንደሚበዙ ተስፋ ሰጠው። አብራምም በእግዚአብሔር ተስፋ አመነ። አብራምም በእግዚአብሔር ተስፋ በማመኑ ምክንያት ጻድቅ ሆኖ ተቈጠረ።

እግዚአብሔርም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ቃል ኪዳን በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው። እግዚአብሔርም አብራምን ‹‹ከገዛ አብራክህ ልጅ እሰጥሃለሁ። የከነዓንንም ምድር ለዘሮችህ እሰጣለሁ›› አለው። አብራም ግን በዚያን ጊዜ ልጅ አልነበረውም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 11-15
5. የተስፋው ልጅ

አብራምና ሦራ ከነዓን ከደረሱ ከዐሥር ዓመታት በኋላ እንኳ ልጅ አልነበራቸውም። ስለዚህም የአብራም ሚስት ሦራ እንዲህ አለችው ‹‹እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ ስለከለከለኝና እኔም ከእንግዲህ እንዳልወልድ ስላረጀሁ አገልጋዬ አጋር ይህችትልህ፤ አግባትና ለኔ ልጅ ትውለድለኝ›› አለችው።

ስለዚህ አብራም አጋርን አገባት። አጋርም ወንድ ልጅ ወለደች። አብራምም ‹‹እስማኤል›› ሲል ስም አወጣለት። ይሁን እንጂ ሦራ በአጋር ቀናችባት። እስማኤል ዐሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነው እግዚአብሔር ለአብራም እንደገና ተናገረው።

እግዚአብሔርም አብራምን ‹‹እኔ ኤልሻዳይ አምላክ ነኝ፤ ካንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ›› አለው። አብራምም በግምባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እግዚአብሔርም አብራምን አለው ‹‹አንተ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። የከነዓንን ምድር ለአንተና ለዘርህ ርስት አድርጌ እሰጥሃለው። እኔም ለዘላለም አምላካቸው እሆናለሁ። አንተም በቤተ ሰብህ የሚገኘውን ወንድ ሁሉ መግረዝ አለብህ›› አለው።

እግዚአብሔርም ‹‹ሚስትህ ሦራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች። እርሱም የተስፋው ልጅ ይሆናል። ስሙን ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ። ኪዳኔንም ከእርሱ ጋር አደርጋለሁ። እርሱም ታላቅ ሕዝብ ይሆናል። እስማኤልንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃል ኪዳኔ ከይስሐቅ ጋር ይሆናል›› አለው። እግዚአብሔርም የአብራምን ስም ‹‹አብርሃም›› ሲል ለወጠለት፤ ትርጓሜውም ‹‹የብዙዎች አባት›› ማለት ነው። እግዚአብሔር የሦራንም ስም ‹‹ሣራ›› ሲል ለወጠላት፤ ትርጓሜውም ‹‹ልዕልት›› ማለት ነው።

በዚያኑ ዕለት አብርሃም በቤተ ሰቡ የሚኙትን ወንዶች ሁሉ ገረዘ። ከዓመት በኋላ አብርሃም 100 ዓመት ሲሆነውና ሣራ 90 ዓመት በሆናት ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። እግዚአብሔርም እንዳላቸው ‹‹ይስሐቅ›› ሲሉ ስም አወጡለት።

ይስሐቅ ወጣት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር የአብርሃምን እምነት እንዲህ ሲል ፈተነው፤ ‹‹አንድዬ ልጅህን ይስሐቅን ውሰድና ለኔ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብልኝ›› አለው። እንደ ገና አብርሃም እግዚአብሔርን ታዘዘና ልጁን ሊሠዋው ተዘጋጀ።

አብርሃምና ይስሐቅ መሥዋዕት ወደሚደረግበት ስፍራ በመጓዝ ላይ ሳሉ ይስሐቅ አባቱን ‹‹አባቴ ሆይ ለመሥዋዕት ማቅረቢያ እንጨቱ ይኸውና፤ በጉ ግን የታለ?›› ሲል ጠየቀ። አብርሃምም ‹‹ልጄ ሆይ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ሲል መለሰለት።

ወደ መሥዋዕት ማቅረቢያ ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን አስሮ በመሠዊያው ላይ አጋደመው። አብርሃምም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን ባነሣ ጊዜ፤ እግዚአብሔር “ተው፤ በልጁ ላይ ምንም ጉዳት አታድርስበት። አንድዬ ልጅህን ሳትሳሳ ለእኔ በመስጠትህ እኔን እንደምትፈራኝ አሁን አውቄአለሁ” አለው።

በአቅራቢያው አብርሃም በቊጥቋጦ ውስጥ የታሰረ በግ አየ። እግዚአብሔር በይስሐቅ ፋንታ ለመሥዋዕት የሚሆን በግ አዘጋጅቶ ነበር። አብርሃምም በደስታ በጉን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ።

እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፣ ‹‹አንድያ ልጅህን እንኳ ሳይቀር ያለህን ሁሉ ልትሰጠኝ ፍቃደኛ ነህና ልባርክህ ቃል እገባለሁ። ዘሮችህ ከሰማይ ክዋክብት ይልቅ ይበዛሉ፤ እኔን ስለ ታዘዝከኝ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 16-22፡፡
6. እግዚአብሔር ለይስሐቅ ሚስት አዘጋጀለት

አብርሃም በጣም ባረጀ ጊዜ ይስሐቅ ዕድሜው ለአቅመ አዳም ደረሰ። ስለዚህ አብርሃም ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ዘመዶቹ ምድር ሄዶ ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት ላከው።

አገልጋዩም የአብርሃም ዘመዶች ወደሚኖሩበት ምድር ከረጅም ጒዞ በኋላ ደረሰ። እግዚአብሔርም የተላከውን የአብርሃምን አገልጋይ ወደ ርብቃ መራው። ርብቃ የአብርሃም ወንድም የልጅ ልጅ ነበረች።

ርብቃ ቤተ ሰቦቿን ትታ ከአገልጋዩ ጋር ወደ ይስሐቅ ቤት ለመሄድ ተስማማች። እንደ ደረሰችም ይስሐቅ አገባት።

ከረጅም ጊዜ በኋላ አብርሃም ሲሞት እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው የተስፋ ቃል ኪዳን ሁሉም ወደ ይስሐቅ ተላለፈ። እግዚአብሔር ለአብርሃም ማንም ሊቆጥር የማይችል ዘር እንደሚኖረው ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ የይስሐቅ ሚስት ርብቃ ልጅ ልትወልድ አልቻለችም።

ይስሐቅ እግዚአብሔርን ለመነ፣ እግዚአብሔርም ርብቃ መንታ ልጆችን እንድታረግዝ ፈቀደ። ሁለቱ ልጆች በርብቃ ማኅፀን ሳሉ እርስ በርሳቸው ይታገሉ ነበር። ርብቃም በማኅፀንዋ እየሆነ ያለው ምን እንደሆነ እግዚአብሔርን ጠየቀች።

እግዚአብሔርም ርብቃን አላት፣ ‹‹በማኅፀንሽ ካሉት ከሁለቱ ልጆችሽ ሁለት ሕዝቦች ይወጣሉ። እነርሱም እርስ በርሳቸው ይታገላሉ። ታላቁም ታናሹን ያገለግላል›› አላት።

የርብቃ ልጆች በተወለዱ ጊዜ ታላቁ ልጅ ቀይና ፀጉራም ሆኖ ወጣ፤ ‹ኤሳው› ሲሉትም ስም አወጡለት፤ ታናሹም ልጅ የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ስሙንም ‹ያዕቆብ› ሲሉ አወጡለት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 24፡1-25፤ 26፡፡
7. እግዚአብሔር ያዕቆብን ባረከ

ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ ያዕቆብ በቤት መቆየትን ይወድ ነበር። ኤሳው ግን አደን ማደን ይወድ ነበር። ርብቃ ያዕቆብን ትወድደው ነበር፣ ይስሐቅ ግን ኤሳውን ይወድደው ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን ኤሳው ከአደን ተመልሶ ሲመጣ በጣም ተርቦ ነበር። ኤሳው ያዕቆብን ‹‹እባክህ ካዘጋጀኸው ምግብ ትንሽ ስጠኝ›› አለው። ያዕቆብም “በመጀመሪያ የብኩርናህን መብት ስጠኝ” ሲል መለሰለት። ስለዚህም ኤሳው የብኩርናውን መብት ለያዕቆብ ሰጠው። ከዚያም ያዕቆብ ከሠራው ምግብ ሰጠው።

ይስሐቅ ኤሳውን ሊባርከው ፈለገ። ነገር ግን ይህን ከማድረጉ በፊት ርብቃና ያዕቆብ ይስሐቅን አታለሉት። ያዕቆብ ኤሳውን መስሎ ወደ ይስሐቅ ቀረበ።በዚያ ጊዜ ይስሐቅ አርጅቶ ነበር፤ ማየትም አይችልም ነበር። ስለዚህም ያዕቆብ የኤሳውን ልብሶች ለብሶ የፍየል ለምድ በአንገቱና በእጆቹ አድርጎ ወደ ይስሐቅ በመቅረብ ይስሐቅን አታለለው።

ያዕቆብ ወደ ይስሐቅ መጣና እንዲህ አለው፣ ‹‹እኔ ኤሳው ነኝ፤ መጥቻለውና ባርከኝ››አለው። ይስሐቅ የፍየሉን ፀጉር ዳሰሰና የልብሱንም ጠረን አሽትቶ ኤሳው እንደ ሆነ አሰበና ባረከው።

ያዕቆብ የብኵርና መብቱንና በረከቱን አታልሎ ስለ ወሰደበት ኤሳው ያዕቆብን ጠላው። አባታቸው ሲሞት ሊገድለውም አቀደ።

ነገር ግን ርብቃ የኤሳውን እቅድ ሰማች። ስለዚህም እሷና ይስሐቅ ከዘመዶቹ ጋር እንዲኖር ወደ ሩቅ አገር ያዕቆብን ሰደዱት።

ያዕቆብ ለረዥም ዓመታት ከርብቃ ዘመዶች ጋር ኖረ። በዚያም ጊዜ ትዳር መስርቶ 12 ወንዶች ልጆችና 1 ሴት ልጅ ወለደ። እግዚአብሔርም በጣም አበለጸገው።

በከነዓን ከኖረበት ከሃያ (20) ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ከቤተ ሰቡ፣ ከአገልጋዮቹና ከመንጋው ሁሉ ጋር ወደ ከነዓን ምድር ተመለሰ።

ኤሳው አሁንም ሊገድለኝ ያስብ ይሆናል ብሎ በልቡ ስላሰበ ያዕቆብ እጅግ በጣም ፈራ። ስለዚህም የእጅ መንሻ እንዲሆነው የብዙ ከብቶች መንጋ ስጦታ አድርጎ ለኤሳው ላከለት። ከብቶቹን ያመጡለት የያዕቆብ አገልጋዮች ኤሳውን ‹‹አገልጋይህ ያዕቆብ እነዚህን ከብቶች ልኮልሃል። እርሱም በቅርቡ ይመጣል›› አሉት።

ኤሳው ግን ቀድሞውኑ ያዕቆብን ይቅር ብሎት ስለ ነበር ዳግም ለመገናኘት በመብቃታቸው ደስ አለው። ያዕቆብ በከነዓን ምድር በሰላም ኖረ፤ ከዚያም ይስሐቅ ሞተ። ያዕቆብና ኤሳውም ቀበሩት። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለት የቃል ኪዳኑ ተስፋ አሁን ከይስሐቅ ወደ ያዕቆብ ተላለፈ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 25፡27-33፡20፡፡
8. እግዚአብሔር ዮሴፍንና ቤተ ሰቡን አዳነ

ከብዙ ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ባረጀ ጊዜ የከብቶቹን መንጋ የሚጠብቁት ልጆቹ እንዴት እንዳሉ እንዲያያቸው የሚወደው ልጁን ዮሴፍን ወደ ወንድሞቹ ላከው።

አባታቸው ያዕቆብ ዮሴፍን ከወንድሞቹ ሁሉ አብዝቶ ይወድደው ስለ ነበረና አለቃቸው እንደሚሆንም ሕልም አልሞ ስለ ነበር ዮሴፍን ወንድሞቹ ጠሉት። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በመጣ ጊዜ ጠልፈው ለባሪያ ነጋዴዎች ሸጡት።

የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ቤት ከመመለሳቸው በፊት የዮሴፍን ልብስ ቀድደው በፍየል ደም ነከሩት። ከዚያም ዮሴፍን አውሬ በልቶታል ብለው በደም የተነከረውን የዮሴፍን ልብስ ለአባታቸው አሳዩት። ያዕቆብም በጣም አዘነ።

የባሪያ ነጋዴዎቹ ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። በዚያን ጊዜ ግብፅ በአባይ ወንዝ አጠገብ የምትገኝ ታላቅና ኃያል አገር ነበረች። የባሪያ ነጋዴዎቹ ዮሴፍን ባርያ አድርገው ለሀብታም የመንግሥት ባለ ሥልጣን ሸጡት። ዮሴፍ ጌታውን በደንብ አድርጎ አገለገለው። እግዚአብሔርም ዮሴፍን ባረከው።

ነገር ግን የጌታው ሚስት ከዮሴፍ ጋር ለመተኛት ፈልጋ ሞከረች። ዮሴፍ ግን በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት አልሠራም ሲል እምቢ አላት። እሷም ስለ ተናደደችበት በሐሰት ከስሳው ተይዞ ወደ እሥር ቤት ተወሰደ። በእሥር ቤትም ቢሆን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ እግዚአብሔር ባረከው።

ምንም እንኳ ዮሴፍ ንጹሕ ሰው ቢሆንም ከሁለት ዓመት በኋላ አሁንም በእሥር ቤት ነበር። አንድ ሌሊት ግብፃውያን ‹ፈርዖን› የሚሉት ንጉሣቸው በጣም የታወከባቸውን ሁለት ሕልሞች አለመ። ከአማካሪዎቹ አንዳቸውም የሕልሙን ትርጕም ሊነግሩት አልቻሉም።

እግዚአብሔር ለዮሴፍ ሕልም የመተርጐም ችሎታ ሰጥቶት ነበር። ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን ከእሥር ቤት ወደ ራሱ አስመጣው። ዮሴፍ ሕልሞቹን ተረጐመለትና እንዲህ አለው። ‹‹እግዚአብሔር ሰባት የጥጋብ ዓመታትን ይልካል፣ ቀጥሎም ሰባት የረሀብ ዓመታት ይሆናሉ›› አለ።

ፈርዖንም በዮሴፍ በጣም ስለተደሰተ በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ከእርሱ ቀጥሎ ሁለተኛ ባለ ሥልጣን አድርጎ ሾመው።

ዮሴፍም ሕዝቡን በሰባቱ የመልካም ምርት ዓመታት በርካታ እህል በጎተራው እንዲያከማቹ ነገራቸው። የሰባቱ የረሀብ ዓመታት በመጡ ጊዜ ዮሴፍ ከጎተራው ለሕዝቡ እህል በመሸጡ በቂ የሚበላ ምግብ አገኙ።

የረሀቡ አስከፊነት በግብፅ ብቻ ሳይሆን ያዕቆብና ቤተ ሰቡ በሚኖሩበት በከነዓን ምድርም ደግሞ ነበር።

ስለዚህ ያዕቆብ ልጆቹ እህል እንዲሸምቱ ወደ ግብፅ ላካቸው። የዮሴፍ ወንድሞች ለእህል ሸመታ ሄደው በፊቱ በቆሙ ጊዜ ዮሴፍ መሆኑን አላስተዋሉትም። ዮሴፍ ግን አወቃቸው።

ዮሴፍ ወንድሞቹን ተለውጠው እንደ ሆነ ለማየት ከፈተናቸው በኋላ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹አትፍሩ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። ለባርነት ስትሸጡኝ ክፉ ልታደርጉብኝ ሞከራችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ክፉውን ለመልካም አደረገው። መጥታችሁ በግብፅ ኑሩ፤ እኔም ለእናንተና ለቤተ ሰቦቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን አቀርብላችኋለሁ።››

የዮሴፍ ወንድሞች ወደ አገራቸው ተመልሰው ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ለአባታቸው ለያዕቆብ በነገሩት ጊዜ ያዕቆብ በጣም ደስ አለው።

ምንም እንኳ ያዕቆብ ሽማግሌ ቢሆንም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር ወደ ግብፅ ሄዶ በዚያ ኖሩ። ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት ልጆቹን እያንዳንዳቸውን ባረካቸው።

እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባቸው የቃል ኪዳን ተስፋዎች ከአብርሃም ወደ ይስሐቅ ተላለፉ፤ ከዚያም ወደ ያዕቆብ፣ ቀጥሎም ወደ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆቹና ቤተ ሰቦቻቸው ተላለፈ። የዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ዘሮቻቸው ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ሆኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 37-50፡፡
9. እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው

ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ዘመዶቹ በሙሉ በግብፅ ኖሩ። እነርሱና ዘሮቻቸው ለብዙ ዓመታት እዚያ መኖራቸውን ቀጠሉ፤ ብዙ ልጆችንም አፈሩ፤ እስራኤላውያንም ተብለው ተጠሩ።

ከመቶዎች ዓመታት በኋላ የእስራኤላውያን ቊጥር እየበዛ መጣ። ግብፃውያንም ዮሴፍንና እነርሱን ለመርዳት ዮሴፍ ያደረገውን ሁሉ ረሱ። እስራኤላውያን እየበዙ በመምጣታቸው ግብፃውያን ፈሯቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ ግብፅን ያስተዳድር የነበረው ፈርዖን እስራኤሎችን ለግብፃውያን ባሪያዎች እንዲሆኑ አደረጋቸው።

ግብፃውያን እስራኤላውያንን የግንብ ሥራ እንዲሠሩና፣ ከተማዎችን ሁሉ እንዲገነቡ በኃይል ያስገድዷቸው ነበር። ከባዱ ሥራም ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አደረገው። እግዚአብሔር ግን ባረካቸው፤ ብዙ ልጆችም ነበሯቸው።

ፈርዖን እስራኤላውያን ብዙ ሕፃናት እንዳሏቸው አየ፤ ስለዚህ ፈርዖን ከእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ሲወለዱ አባይ ወንዝ ውስጥ በመወርወር እንዲገድሉ ሕዝቡን አዘዘ።

በዚያን ጊዜ አንዲት እስራኤላዊት ሴት ወንድ ልጅ ወለደች። እርሷና ባለቤቷ የቻሉትን ያህል ልጁን ለመደበቅ ሞከሩ።

የልጁ ወላጆች ልጁን ከዚያ በላይ ሊደብቁት እንደማይችሉ በተረዱ ጊዜ ልጁ እንዳይሞት በሚንሳፈፍ ቅርጫት ውስጥ አድርገው በአባይ ወንዝ ዳር ባለው ቄጤማ ውስጥ ወንዙ ላይ እንዲንሳፈፍ ለቀቁት። ታላቅ እህቱም በልጁ ላይ የሚደርስበትን ለማየት በቅርብ ትከታተለው ነበር።

የፈርዖን ሴት ልጅ ቅርጫቱን አየችና በውስጡ ያለውን ተመለከተች። ሕፃኑን ባየች ጊዜ እንደ ልጇ አድርጋ ወሰደችው። እርሷም ልጁን ጡት የምታጠባ እስራኤላዊት ሴት ቀጠረች። የቀጠረቻትም ሴትዮ የልጁ እናት መሆኗን አላወቀችም ነበር። ልጁም አድጎ የናቱን ጡት መጥባት ባቆመ ጊዜ ሴትዮዋ ወደ ፈርዖን ልጅ መለሰችው። የፈርዖ ልጅም ስሙን ‹‹ሙሴ›› ብላው ጠራች።

ሙሴም ባደገ ጊዜ አንድ ቀን አንድ ግብፃዊ እስራኤላዊ የሆነውን ባሪያ ሲመታው አየ። ሙሴም እስራኤላዊ ወገኑን ሊያድነው ፈለገ።

ሙሴ ማንም ሰው ያላየ መስሎት ግብፃዊውን ገድሎ ቀበረው። ነገር ግን ሙሴ ያደረገውን አንድ ሰው አይቶት ነበር።

ሙሴ ያደረገውን ፈርዖን በሰማ ጊዜ ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ወታደሮች ነፍሱን ለማዳን ወደ ምድረ በዳ ሸሸ።

ሙሴ ከግብፅ ምድር ርቆ ወደሚገኝ ምድረ በዳ በመሄድ የበጐች እረኛ ሆነ። ከዚያም አገር ሚስት አግብቶ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ።

አንድ ቀን ሙሴ በጐቹን እየጠበቀ ሳለ እሳት የሚነድበት ቊጥቋጦ ተመለከተ፤ ይሁን እንጂ ቊጥቋጦው አይቃጠልም ነበር። ሙሴም በደንብ ለማየት ወደ ቊጥቋጦው ጠጋ አለ። ወደሚቃጠለው ቊጥቋጦ ጠጋ ሲል የእግዚአብሔር ድምፅ ‹‹ሙሴ፤ በቅዱስ ስፍራ ቆመሃልና ከእግርህ ጫማህን አውልቅ›› አለው።

እግዚአብሔርም ‹‹የሕዝቤን ሥቃይ አይቻለሁና እስራኤልንም ከግብፅ ባርነት ነጻ እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለው። ለአብርሃም፣ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተስፋ የሰጠኋቸውን የከነዓንን ምድር እሰጣቸዋለሁ አለ።››

ሙሴም ሕዝቡ ‹‹ማን ላከህ›› ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ ያለሁና የሚኖር ንኝ፤ ስለዝህ ‹ያለና የሚኖር ልኮኛል› ብለህ ንገራቸው›› አለው። ደግሞሜ ‹‹እኔ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ያህዌህ ነኝ። ስሜም ለዘላለም ይህ ነው” አለው።

ሙሴ ስለ ፈራ ወደ ፈርዖን መሄድ አልፈለገም። ምክንያቱም የንግግር ችሎታ የለኝም ብሎ በማሰቡ ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር የሙሴን ወንድም አሮንን አብሮት እንዲሄድና ሙሴን እንዲረዳው ላከው። እግዚአብሔርም ፈርዖን ሕዝቡን አለቅም በሚል ልቡን ሊያደነድን እንደሚችል ሙሴንና አሮንን አስጠነ ቃቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 1-4፡፡
10. ዐሥሩ መቅሠፍቶች

ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው “የእስራኤል አምላክ “ሕዝቤን ልቀቅ! ይልሃል” አሉት። ፈርዖን ግን አልሰማቸውም። እስራኤላውያን ነጻ ሆነው እንዲሄዱ በመልቀቅ ፈንታ ከበፊቱ የከበደ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው!

ፈርዖን ሕዝቡን አልለቅም ማለቱን ቀጠለ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ዐሥር መቅሠፍቶችን ላከ። እግዚአብሔር በእነዚህ መቅሠፍቶች አማካይነት ከፈርዖንና ከግብፅ አማልክት ሁሉ ይልቅ ኃያል መሆኑን ለፈርዖን ዐሳየው።

እግዚአብሔር የዓባይን ውሃ ወደ ደም ለወጠው፣ ነገር ግን ፈርዖን አሁንም እስራኤላውያንን እንዲሄዱ አልለቀቃቸውም።

እግዚአብሔር በግብፅ ሁሉ ላይ እንቁራሪቶችን ላከ። ፈርዖን እንቁራሪቶቹን እንዲያርቅ ሙሴን ለመነው። እንቁራሪቶቹ ሁሉ ከሞቱ በኋላ ግን ፈርዖን ልቡን እንደገና አደነደነና እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲወጡ አልለቀቃቸውም።

ስለዚህ እግዚአብሔር የቅማል መቅሰፍት ላከ። ከዚያም የዝንብ መቅሰፍት ላከ። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠራና መቅሠፍቱን ካቆሙ እስራኤላውያን ከግብፅ መሄድ እንደሚችሉ ነገራቸው። ሙሴ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር የዝንብ መቅሰፍቶችን ሁሉ ከግብፅ አስወገደ። ነገር ግን ፈርዖን ልቡን አደነደነና ሕዝቡን ነፃ እንዲወጡ አልለቀቃቸውም።

ቀጥሎ እግዚአብሔር የግብፃውያን ከብቶች ሁሉ ታመው እንዲሞቱ አደረገ። ነገር ግን የፈርዖን ልብ ስለደነደነ እስራኤላውያንን አልለቀቀም።

ከዚያም እግዚአብሔር በፈርዖን ፊት ዐመድ ወደ ሰማይ እንዲበትን ለሙሴ ነገረው። ዐመዱን በበተነ ጊዜ በግብፃውያን ላይ የሚያም ቊስል ሆነባቸው፣ በእስራኤላውያን ላይ ግን ቊስሉ አልሆነባቸውም። እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ ስላደነደነ ፈርዖን እስራኤላውያንን አልለቀቀም።

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በግብፅ ያለውን አብዛኛውን ቡቃያ ያሚያጠፋና ከቤት ውጪ የነበረውን ማንኛውንም ሰው የሚገድል በረዶ ላከ። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፣ ‹‹በድዬአለሁ። መሄድ ትችላላችሁ›› ብሎ ነገራቸው። ስለዚህ ሙሴ ጸለየ፣ በረዶውም ከሰማይ መዝነቡን አቆመ።

ነገር ግን ፈርዖን እንደ ገና ኃጢአት ሠራ፤ ልቡንም አደነደነ። እስራኤላውያንን አልለቀቀም።

ስለዚህ እግዚአብሔር በግብፅ ላይ የአንበጣዎችን መንጋ አመጣ። እነዚህ አንበጣዎች ከበረዶው የተረፈውን ሰብል ሁሉ አወደሙት።

ከዚያም እግዚአብሔር ለሦስት ቀን የቆየ ጨለማ ላከ። ጭለማው በጣም ከባድ ስለነበር ግብፃውያን ከቤታቸው ሊወጡ አቻሉም ነበር። እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ግን ብርሃን ነበረ።

ከእነዚህ ዘጠኝ መቅሠፍቶች በኋላ እንኳ ፈርዖን አሁንም እስራኤላውያንን አልለቅም አለ። ፈርዖን መስማት እንቢ ስላለ፣ እግዚአብሔር አንድ የመጨረሻ መቅሠፍት ለመላከ ወሰነ። ይህ መቅሰፍት ፈርዖን ዐሳቡን እንዲቀይር ያደርጋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 5-10፡፡
11. ፋሲካ

ፈርዖን እስራኤላውያንን ካልለቀቀ የግብፃውያን ሰዎችና የእንስሳቶቻቸውን መጀመሪያ የተወለዱትን ወንዶች ሁሉ እንደሚገድል እግዚአብሔር ፈርዖንን አስጠነቀቀው። ፈርዖን ይህን ቢሰማም እንኳ፣ አሁንም ማመንና ለእግዚአብሔር መታዘዝ እምቢ አለ።

እግዚአብሔር በእርሱ ያመነ የማንኛውንም ሰው የመጀመሪያ ወንድ ልጅን ለማዳን መንገድ አዘጋጀ። እያንዳንዱ ቤተ ሰብ ፍጹም የሆነ የበግ ጠቦት መርጦ እንዲያርድ አዘዘ።

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የጠቦቱን ደም በቤታቸው በር ላይ እንዲቀቡት፣ ሥጋውንም ጠብሰው ያለ እርሾ ከተጋገረው ቂጣ ጋር በፍጥነት እንዲበሉት ነገራቸው። ደግሞ በበሉት ጊዜ ከግብፅ ለመውጣት እንዲዘጋጁ ነገራቸው።

እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር አደረጉ። እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር በመላው ግብፅ አልፎ መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ገደለ።

የእስራኤላውያን ቤቶች ሁሉ በሮቻቸው ደም ተቀብተው ነበር፣ ስለዚህ እግዚአብሔር በቤቶቹ አለፈ። በቤቶቹ ውስጥ የነበረው ሁሉ ከሞት ተረፈ። እስራኤላውያን በጠቦቱ ደም ምክንያት ዳኑ።

ግብፃውያን ግን በእግዚአብሔር አላመኑም፣ ትእዛዛቱንም አልፈጸሙም። ስለዚህ እግዚአብሔር በቤቶቻቸው አላለፈም። እግዚአብሔር የግብፃውያንን በመጀመሪያ የተወለዱ ወንዶችን በሙሉ ገደለ።

በእስር ቤት ካለው በኵር ልጅ ጀምሮ እስከ ፈርዖን በኩር ልጅ ድረስ የግብፃዊያን የመጀመሪያ ወንድ ልጅ በሙሉ ሞተ። ከጥልቅ ሐዘናቸው የተነሣ በግብፅ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ያለቅሱና ይጮኹ ነበር።

በዚያው ሌሊት ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፣ “እስራኤላውያንን ይዛችሁ አሁኑኑ ከግብፅ ውጡ” አላቸው። ግብፃውያንም እስራኤላውያን በፍጥነት ከግብፅ እንዲወጡ አስቸኰሉአቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 11፡1-12፡32፡፡
12. የእስራኤላውያን ከግብፅ መውጣት

እስራኤላውያን ከግብፅ በመውጣታቸው በጣም ደስ አላቸው። ከእንግዲህ ባሪያዎች አይደሉም፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድርም በመጓዝ ላይ ናቸው። ግብፃውያን ለእስራኤላውያን ወርቅና ብር ሌሎችም የከበሩ ነገሮች ሳይቀሩ የጠየቁትን ማንኛውንም ነገር ሰጡአቸው። እስሬላውያን ከግብፅ ሲወጡ ከሌሎች ብሔሮች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች በእግዚአብሔር አምነው ከእስራኤላውያን ጋር ከግብፅ ወጡ።

እግዚአብሔርም ቀን ረጅም በሆነ የደመና ዓምድ፣ ማታ ደግሞ ረጅም የሆነ የእሳት ዓምድ ከፊት ከፊታቸው እንዲሄድ እያደረገ መራቸው። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር በመሆን ሲጓዙ መራቸው።እነርሱ ማድረግ ያለባቸው ነገር ቢኖር እርሱን መከተል ብቻ ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ፈርዖንና ሕዝቡ ዐሳባቸውን ቀይረው እስራኤላውያን እንደ ገና የእነርሱ ባሪያዎች እንዲሆኑ ፈለጉ። እግዚአብሔር ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን ሕዝቡ እንዲያዩ፣ እንዲሁም እርሱ፣ ያሕዌ፣ ከፈርዖንና ከአማልክቱ የበለጠ ኃያል እንደ ሆነ ይረዱ ዘንድ የፈርዖንን ልብ አደነደነው።

ስለዚህ ፈርዖንና ጦር ሠራዊቱ እንደ ገና ባሪያዎቻቸው ሊያደርጉአቸው እስራኤላውያንን አሳደዱአቸው። እስራኤላውያን የግብፅ ጦር ሠራዊት ሲመጣ ባዩ ጊዜ፣ በፈርዖን ጦር ሠራዊትና በቀይ ባሕር መካከል እንደ ተጠመዱ ዐወቁ። በጣም ፈርተው ስለ ነበር፣ ‹‹ከግብፅ ለምን ወጣን? መሞታችን ነው!›› ብለው ጮኹ።

ሙሴ እስራኤላውያንን፣ ‹‹አትፍሩ! ዛሬ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ተዋግቶ ያድናችኋል›› ብሎ ነገራቸው። ከዚያም እግዚአብሔር፣ለሙሴ ‹‹ሕዝቡ ወደ ቀይ ባሕር እንዲንቀሳቀሱ ንገራቸው››አለ።

ከዚያም ግብፃውያን እስራኤላውያንን ማየት እንዳይችሉ እግዚአብሔር የደመናውን ዓምድ በእስራኤላውያንና በግብፃውያን መካከል አደረገው።

እግዚአብሔርም ለሙሴ በባሕሩ ላይ እጁን እንዲዘረጋና ውሃውን እንዲከፍለው ነገረው። ከዚያም እግዚአብሔር በባሕሩ መካከል መተላለፊያ መንገድ ይኖር ዘንድ ነፋስ ውሃውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ እንዲገፋ አደረገ።

እስራኤላውያንም ውሃው በግራና በቀኛቸው እንደ ግድግዳ ሆኖላቸው በባሕሩ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ተጓዙ።

ከዚያም እግዚአብሔር እስራኤላውያን እያመለጡ መሆናቸውን ግብፃውያኑ ያዩ ዘንድ የደመናውን አምድ ከመንገዱ ወደ ላይ አነሳው። ግብፃውያንም ከኋላቸው ሊያሳድዱአቸው ወሰኑ።

ስለዚህ በባሕሩ መካከል ውስጥ ባለው መንገድ እስራኤላውያንን ተከተሉአቸው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ግብፃውያን እንዲርበተበቱና ሰረገሎቻቸውም እንዳይንቀሳቀሱ አደረገ።ግብፃውያንም “ለነፍሳቸው ሽሹ! እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው ነው!” ብለው ጮኹ።

እስራኤላውያን ሁሉ ባሕሩን በደኅና ከተሻገሩ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና እጁን እንዲዘረጋ ለሙሴ ነገረው። እርሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘ ባደረገ ጊዜ፣ ውሃው በግብፃውያን ሠራዊት ላይ ተገለበጠና ወደ ድሮው ቦታ ተመለሰ።የግብፃውያን ጦር ሠራዊት በሙሉ ሰጠመ።

እስራኤላውያን ግብፃውያን እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ በእግዚአብሔር አመኑ፤ ሙሴም የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑን አመኑ።

ደግሞም እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከሞትና ከባርነት ስለ አዳናቸው እጅግ በጣም ደስ አላቸው! አሁን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነጻ ሆኑ። እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ከግብፃውያን ጦር ሠራዊት ስለ አዳናቸው ዐዲሱን ነጻነታቸውን ለማክበርና እግዚአብሔርን ለማመስገን ብዙ መዝሙሮችን ዘመሩ።

እግዚአብሔር እንዴት በግብፃውያን ላይ ድልን እንደ ሰጣቸውና ከባርነት እንዳዳናቸው ያስታውሱ ዘንድ በያመቱ ፋሲካን እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን አዘዛቸው። እንከን በፍጹም የሌለበትን ጠቦት አርደው ካልቦካ ቂጣ ጋር በመብላት ተደሰቱ።፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 12፡33-15፡21፡፡
13. እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በቀይ ባሕር ውስጥ ካሳለፋቸው በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ ሲና ተብሎ ወደሚጠራ ተራራ ወሰዳቸው። ይህም ሙሴ የሚቃጠለውን ቊጥቋጦ ያየበት ተራራ ነው። ሕዝቡ በተራራው ሥር ድንኳኖቻቸውን ተከሉ።

እግዚአብሔርም፣ ‹‹ለእኔ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ፣ የከበረ ርስት፣ የካህናት መንግስት፣ እንዲሁም ቅዱስ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ›› ብሎ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ተናገረ።

ሕዝቡ በመንፈሳዊነት ራሳቸውን ካዘጋጁ ከሦስት ቀን በኋላ፣ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፣ በመብረቅ፣ በጢስ እንዲሁም ከፍ ባለ የመለከት ድምፅ በሲና ተራራ ላይ ወረደ። ወደ ተራራው እንዲወጣ የተፈቀደለት ሙሴ ብቻ ነበር።

ከዚያም እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ገባላቸውና እንዲህ አለ፣ ‹‹እኔ ከግብፅ ባርነት ያዳንኳችሁ፣ አምላካችሁ፣ ያህዌ ነኝ። ሌሎችን አማልክት አታምልኩ።››

‹‹ጣዖታትን አትሥሩ አታምልኳቸውም፣ ምክንያቱም እኔ፣ ያህዌ ቀናተኛ አምላከ ነኝ። ስሜንም በከንቱ አትጥሩ፣ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ዐስብ። ይኸውም ሥራህን ሁሉ በስድስት ቀን ሥራ፣ ሰባተኛው ቀን ግን የምታርፍበትና እኔን የምታስታውስበት ዕለት ነው።››

‹‹አባትህንና እናትህን አክብር። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። አትዋሽ። የባልንጀራህን ሚስት፣ ቤቱን፣ ወይም የእርሱ የሆነውን ማንኛውም ነገር አትመኝ።››

ከዚያም እግዚአብሔር እነዚህን ዐሥር ትእዛዛት በሁለት ጠፍጣፋ ድንጋዮች ላይ ጽፎ ለሙሴ ሰጠው። ደግሞ እግዚአብሔር የሚከተሉአቸውን ሌሎች ብዙ ሕግጋትንና ደንቦችን ሰጣቸው። ሕዝቡ እነዚህን ሕግጋት ከታዘዙ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸውና እንደሚጠብቃቸው ተስፋ ሰጣቸው። ሕግጋቱን ካልታዘዙ ግን እግዚአብሔር ይቀጣቸዋል።

ደግሞም እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲሠሩለት ስለሚፈልገው ድንኳን ዝርዝር መግለጫ ሰጣቸው። እርሱ የመገናኛው ድንኳ ተብሎ ይጠራ ነበር፣ በትልቅ መጋረጃ የተከፈሉ ሁለት ክፍሎችም ነበሩት። እግዚአብሔር በዚያ ይኖር ስለ ነበረ፣ ከመጋረጃ በስተጀርባ ወዳለው ክፍል እንዲገባ የተፈቀደለት ሊቀ ካህን ብቻ ነበር።

የእግዚአብሔርን ሕግ ያልታዘዘ ማንኛውም ሰው በመገናኛው ድንኳ ፊት ለፊት ወዳለው መሠዊያ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚሆን እንስሳ ያመጣ ነበር። ካህኑ እንስሳውን ያርድና በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው ነበር። የተሠዋው እንስሳ ደም የሰውዬውን ኃጢአት ይሸፍንና ሰውዬውን በእግዚአብሔር ፊት ያነጻው ነበር። እግዚአብሔር ካህናቱ ይሆኑ ዘንድ የሙሴን ወንድም አሮንንና፣የአሮንን ዝርያዎች መረጠ።

ሕዝቡ ሁላቸውም እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዛት ለመፈጸም፣ እግዚአብሔርን ብቻ ለማምለክ፣ እንዲሁም የተለዩ ሕዝቡ ለመሆን ተስማሙ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፉኛ ኃጢአት ሠሩ።

ሙሴ ለብዙ ቀናት በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገር ነበር። ሕዝቡ እርሱ እስኪመለስ ድረስ መጠበቅ ሰለቻቸው። ስለዚህ ወደ አሮን ወርቅ አመጡና ጣዖት እንዲሠራላቸው ጠየቁት!

አሮንም በጥጃ ቅርፅ የወርቅ ጣዖት ሠራ። ሕዝቡም ልቅ በሆነ ሁኔታ ጣዖቱን ማምለክ ጀመሩ፣ መሥዋዕትም ሠዉለት! በኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔር በጣም ተቈጣቸው፣ ሊያጠፋቸውም ፈለገ። ነገር ግን ሙሴ ጸለየላቸው፣ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማና አላጠፋቸውም።

ሙሴ ከተራራው ወርዶ ጣዖቱን ስያምልኩ ባየ ጊዜ በጣም ተቈጥቶ እግዚአብሔር ዐሥሩን ትእዛዛት የጻፈባቸውን ድንጋዮች ሰባበረ።

ከዚያም ሙሴ ጣዖቱን ፈጨው፣ በውሃውም ላይ በተነው፣ ለሕዝቡም አጠጣቸው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ መቅሠፍት ላከና ብዙዎቻቸው ሞቱ።

ሙሴ እንደ ገና ተራራው ላይ ወጣና እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር እንዲላቸው ጸለየ። እግዚአብሔር ሙሴን ሰማውና ይቅር አላቸው። ሙሴ የሰባበራቸውን ለመተካት በዐዲስ ጠፍጣፋ ድንጋዮች ላይ የተጻፉትን ዐሥሩን ትእዛዛት ይዞ ከተራራ ወረደ። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከሲና ተራራ ወደ ተስፋዪቱ ምድር መራቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 19-34፡፡
14. በምድረ በዳ መቅበዝበዝ

እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ክፍል ለሆኑት ሕግጋት እንዲታዘዙ ለእስራኤላውያን ከነገራቸው በኋላ የሲና ተራራን ለቀው ሄዱ። እግዚአብሔርም ሕዝቡን ከሲና ተራራ ከነዓን ተብላ ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ይመራቸው ጀመር። የደመናው ዓምድ ከፊት ለፊታቸው ወደ ከነዓን ሄደ፣ እነርሱም ተከተሉት።

እግዚአብሔር የተስፋዪቱን ምድር ለዘሮቻቸው እንደሚሰጣቸው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር፣ ነገር ግን በዚያች ምድር ብዙ የሕዝብ ወገኖች ይኖሩ ነበር። እነርሱም ከነዓናውያን ተብለው ይጠሩ ነበር። ከነዓናውያን እግዚአብሔርን አያመልኩትም ወይም አይታዘዙትም ነበር።ነገር ግን ሐሰተኞች አማልክትን ያመልኩ ነበር፤ ብዙ ክፉ ነገሮችንም ያደርጉ ነበር።

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሎ ነገራቸው፣ ‹‹በተስፋዪቱ ምድር ያሉትን ከነዓናውያንን ሁሉ አጥፉአቸው። ከእነርሱ ጋር ሰላምን አታድርጉ፤ አታግቡአቸውም። ጣዖቶቻቸውን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው። ለእኔ ባትታዘዙ፣ በእኔ ፈንታ የእነርሱን ጣዖታት ታመልካላችሁ።››

እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ድንበር በደረሱ ጊዜ፣ ሙሴ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ አንድ ሰው፣ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን መረጠ። ሄደው ምድሪቱ ምን እንደምትመስል እንዲሰልሉ መመሪያ ሰጣቸው።ደግሞም ከነዓናውያን ብርቱዎች ወይም ደካሞች መሆናቸውን ለማየት ከነዓናውያንን መሰለል ነበረባቸው።

ዐሥራ ሁለቱ ሰዎች በከነዓን ውስጥ ለአርባ ቀን ተጓዙና ተመልሰው መጡ።መጥተውም ‹‹ምድሪቱ በጣም ለም ነች፤ ሰብሉም የተትረፈረፈ ነው!›› ብለው ለሕዝቡ ነገሩአቸው። ከስችላዮቹ ዐሥሩ ግን፣ ‹‹ከተሞቹ በጣም ብርቱዎች፤ ሰዎቹም ግዙፍ ናቸው! እነርሱን ብንወጋቸው በእርግጥ ያሸንፉናል፤ ይገድሉናልም!›› አሉ።

ወዲያውኑ ሌሎቹ ሁለት ሰላዮች፣ ካሌብና ኢያሱ፣ ‹‹የከነዓን ሰዎች ረጃጅሞችና ብርቱዎች መሆናቸው እውነት ነው፣ ነገር ግን እኛ በእርግጥ እናሸንፋቸዋለን! እግዚአብሔር ስለ እኛ ይዋጋል!›› አሉ።፡

ሕዝቡ ግን ካሌብንና ኢያሱን አልሰሙአቸውም። ሙሴንና አሮንን ተቈጡአቸውና፣ ‹‹ወደዚህ አስከፊ ቦታ ለምን አመጣችሁን? እኛ በጦርነት ከምንሞትና ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ባሮች ከሚሆኑ ይልቅ በግብፅ ብንኖር ይሻለን ነበር›› አሉ። ሕዝቡ ወደ ግብፅ መልሶ የሚወስዳቸውን ሌላ መሪ ለመምረጥ ፈለጉ።

እግዚአብሔር በጣም ተቈጣና ወደ መገናኛው ድንኳ መጣ። እንዲህም አለ፣ ‹‹እናንተ በእኔ ላይ ስላመፃችሁ፣ ሕዝቡ ሁሉ በምድረ በዳ ይቅበዘበዛሉ። ከኢያሱና ከካሌብ በቀር ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሁሉ በዚያ ይሞታሉ እንጂ ከቶ ወደ ተስፋዪቱ ምድር አይገቡም›› አላቸው።

ሕዝቡ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ኃጢአት በመሥራታቸው ዐዘኑ። የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይዘው የከነዓንን ሰዎች ለመውጋት ሄዱ። ሙሴ ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስላልነበረ እንዳይሄዱ አስጠነቀቃቸው፣ ነገር ግን እርሱን አልሰሙትም።

እግዚአብሔር አብሮአቸው ወደ ጦርነቱ አልሄደም፣ ስለዚህ ተሸነፉ፤ ብዙዎቻቸውም ተገደሉ። ከዚያም እስራኤላውያን ከከነዓን ተመለሱና በምድረ በዳ ለአርባ ዓመት ተቅበዘበዙ።

የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ በተቅበዘበዙባቸው አርባ ዓመታት እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ሰጣቸው። ከሰማይ ‹‹መና›› ተብሎ የሚጠራ ምግብ ሰጣቸው። ደግሞም ሥጋ ይበሉ ዘንድ ወደ ሰፈራቸው ድርጭቶችን ላከላቸው። በዚያን ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ልብሳቸውና ጫማቸው እንዳያልቅ አደረገ።

እግዚአብሔር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ውሃ እንኳ ከአለት ሰጣቸው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ አማረሩ፤ አጕረመረሙም። ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለሰጠው ተስፋ አሁንም ታማኝ ነበር።

ሕዝቡ ምንም ውሃ ባልነበራቸው በሌላ ጊዜ እግዚአብሔር ለሙሴ፣ ‹‹አለቱን ተናገረው፣ ከእርሱም ውሃ ይወጣል›› አለው። ነገር ግን ሙሴ ለአለቱ በመናገር ፈንታ በበትር ሁለት ጊዜ ስለ መታው በሕዝቡ ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አላከበረም። ሁለም ሰው እንዲጠጣ ከአለቱ ውሃ ወጣ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በሙሴ ላይ ተቈጣና፣ ‹‹ወደ ተስፋዪቱ ምድር አትገባም›› አለው።

እስራኤላውያን ለአርባ ዓመት በምድረ በዳ ከተቅበዘበዙ በኋላ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁት ሁሉ ሞቱ። ከዚያም እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ገና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ዳርቻ መራቸው። አሁን ሙሴ በጣም አርጅቶ ነበር፣ ስለዚህ ሕዝቡን በመምራት እንዲያግዘው እግዚአብሔር ኢያሱን መረጠ። ደግሞም እግዚአብሔር አንድ ቀን እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እንደሚልክ ለሙሴ ተስፋ ሰጠው።

ከዚያም እግዚአብሔር የተስፋዪቱን ምድር ለማየት ይችል ዘንድ ወደ ተራራ ራስ ላይ እንዲወጣ ለሙሴ ነገረው። ሙሴ የተስፋዪቱን ምድር ዐየ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ እርስዋ እንዲገባ አልፈቀደለትም። ከዚያም ሙሴ ሞተ፣ እስራኤላውያንም ለሠላሳ ቀናት አለቀሱለት። ኢያሱም ዐዲሱ መሪአቸው ሆነ። ኢያሱ በእግዚአብሔር ያመነና ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ ስለ ነበር ጥሩ መሪ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 16-17፤ ዘኍልቁ 10-14፤ 20፤ 27፤ ዘዳግም 34፡፡
15. የተስፋይቱ ምድር

በመጨረሻ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር፣ ወደ ከነዓን የሚገቡበት ጊዜ ደረሰ። ኢያሱ በብርቱ ግንብ ተጠብቃ ወደ ነበረችው የከነዓናውያን ከተማ ወደ ኢያሪኮ ሁለት ሰላዮችን ላከ። በዚያች ከተማ ሰላዮቹን የሸሸገችና ኋላ ላይ እንዲያመልጡ የረዳቻቸው ረዓብ የተባለች ጋለሞታ ትኖር ነበር። እርስዋ ይህን ያደረገችው በእግዚአብሔር ስላመነች ነው። ሰላዮቹ፤ እስራኤላውያን ኢያሪኮን በሚያጠፉበት ጊዜ ረዓብንና ቤተ ሰብዋን እንደሚያድኑአቸው ቃል ገቡላት።

እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር ነበረባቸው። እግዚአብሔር፣ ‹‹መጀመሪያ ካህናቱ እንዲሻገሩ አድርግ›› ብሎ ለኢያሱ ነገረው። ካህናቱ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መግባት በጀመሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በደረቅ መሬት መሻገር ይችሉ ዘንድ ከላይ በኩል ይፈስ የነበረ ውሃ መፍሰሱን አቆመ።

ሕዝቡ የዮርዳኖስን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ፣ እግዚአብሔር ኃይለኛውን የኢያሪኮ ከተማ እንዴት እንደሚያጠፋት ለኢያሱ ነገረው። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታዘዙ። ወታደሮቹና ካህናቱ ልክ እግዚአብሔር እንደ ነገራቸው በቀን አንዴ ለስድስት ቀናት የኢያሪኮን ከተማ ዞሩ።

ከዚያም በሰባተኛው ቀን፣ እስራኤላውያን ሰባት ጊዜ ከተማይቱን ዞሩ። ለመጨረሻ ጊዜ ከተማዪቱን እየዞሩ እያሉ ወታደሮቹ ጮኹ፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ነፉ።

ከዚያም በኢያሪኮ ዙሪያ የነበረው ግንብ ወደቀ! እግዚአብሔር እንዳዘዘው እስራኤላውያን በከተማይቱ የነበረውን ነገር ሁሉ አጠፉ። የእስራኤላውያን ወገን የሆኑትን ረዓብንና ቤተ ሰብዋን ብቻ አዳኑአቸው። በከነዓን የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች እስራኤላውያን ኢያሪኮን እንዳጠፉአት በሰሙ ጊዜ፣ እስራኤላውያን እነርሱንም ደግሞ እንደሚያጥቋቸው በማሰብ ፈሩ።

እግዚአብሔር በከነዓን ካሉ ከማናቸውም የሕዝብ ወገኖች ጋር የሰላም ስምምነት እንዳያደርጉ እስራኤላውያንን አዞአቸው ነበር። ነገር ግን ገባዖናውያን የተባሉት ከከነዓናውያን ሕዝብ ወገኖች አንዱ የሆኑት፣ ከከነዓን ራቅ ብሎ ከሚገኝ ቦታ የመጡ መሆናቸውን ለኢያሱ ዋሽተው ነገሩት። ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት እንዲያደርግ ኢያሱን ጠየቁት። ገባዖናውያን ከየት እንደ ሆኑ ኢያሱና እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አልጠየቁም። ስለዚህ ኢያሱ ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት አደረገ።

ገባዖናውያን እንዳታለሉአቸው ባወቁ ጊዜ እስራኤላውያን ተናደዱ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት የገቡት ቃል ስለ ነበር ከእነርሱ ጋር ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ጠበቁ። ቆየት ብሎ በሌላ ጊዜ፣ በከነዓን የነበሩ አሞራውያን የሚባሉ የሌላ ሕዝብ ወገን ነገሥታት፣ የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ስምምነት እንዳደረጉ ሰሙ፣ ስለዚህ ጦር ሠራዊታቸውን አንድ ላይ አስተባበሩና ገባዖናውያንን ወጉ። ገባዖናውያንም እርዳታ ጥየቃ ወደ ኢያሱ መልእክት ላኩ።

ስለዚህ ኢያሱ የእስራኤልን ጦር ሠራዊት ሰበሰበና ወደ ገባዖናውያን ለመድረስ ሌሊቱን ሙሉ ተጓዙ። በማለዳ ሳያስቡት የአሞራውያንን ጦር ሠራዊት መቱ።

በዚያን ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ተዋጋ። አሞራውያንን አደናገራቸውና ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ ልኮ ከአሞራውያን ብዙዎችን ገደለ።

ደግሞ እግዚአብሔር እስራኤላውያን አሞራውያንን ፈጽመው ለማጥፋት በቂ ጊዜ ይኖራቸው ዘንድ ፀሐይ በሰማይ በአንድ ቦታ እንድትቆም አደረገ። በዚያን ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤል ታላቅ ድል አጐናጸፋቸው።

እግዚአብሔር እነዚያን ጦር ሠራዊት ካጠፉ በኋላ፣ ብዙዎቹ የከነዓናውያን ሕዝብ ወገኖች እስራኤልን ለመውጋት በአንድነት ተሰበሰቡ። ነገር ግን ኢያሱና እስራኤላውያን ወጉና አጠፉአቸው።

ከዚህ ጦርነት በኋላ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ለእስራኤል ነገድ ከተስፋዪቱ ምድር የሚደርሰውን ክፍል ሰጠው። ከዚያም እግዚአብሔር ለእስራኤል በድንበሮችዋ ሁሉ ሰላምን ሰጣት።

ኢያሱ ባረጀ ጊዜ፣ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ አንድ ላይ ጠራ። ከዚያም ኢያሱ እግዚአብሔር በሲና ከእስራኤላውያን ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ሕዝቡ የመታዘዝ ግዴታ እንዳለበቸው አስታወሳቸው። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው ለመኖርና ሕግጋቱን ለመከተል ቃል ገቡ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከኢያሱ 1-24፡፡
16. ነፃ አውጪዎቹ

ኢያሱ ከሞተ በኋላ፣ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አልታዘዙም፤ የቀሩትንም ከነዓናውያን ከመካከላቸው አላስወጡም፤ ወይም የእግዚአብሔርን ሕግ አልታዘዙም። እስራኤላውያን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ያህዌን ከማምለክ ይልቅ የከነዓናውያንን አማልክት ማምለክ ጀመሩ። እስራኤላውያን ንጉሥ አልነበራቸውም፣ ስለዚህ እያንዳንዱ ትክክል መስሎ የሚታየውን ሁሉ ያደርግ ነበር።

እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አለመታዘዛቸውን በመቀጠላቸው፣ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸው እንዲያሸንፏቸው አደረገ። እነዚህ ጠላቶቻቸው የእስራኤላውያንን ሀብት ሁሉ ዘረፉ፣ንብረታቸውንም አወደሙ፣ አብዛኞቻቸውንም ገደሉ። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ባለመታዘዝና በጠላቶቻቸው በመጨቆን ብዙ ዘመናትን ካሳለፉ በኋላ፣ ንስሐ ገቡ፤ እግዚአብሔርንም ከጠላቶቻቸው እንዲያድናቸው ጠየቁ።

ከዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው የሚያድናቸውን ነፃ አውጪ ላከላቸው፤ ለምድሪቱም ሰላምን አመጣ። ነገር ግን ሰዎቹ እግዚአብሔርን እንደገና ረሱ። ጣዖትንም ማምለክ ጀመሩ፤ ስለ ሆነም እግዚአብሔር በአቅራቢያቸው የሚገኙትን ጠላቶቻቸውን ምድያማውያንን አስንሣባቸው፣ አሸነፉአቸውም።

ምድያማውያን የእስራኤላውያንን ሰብል ሁሉ ለሰባት ዓመታት ወሰዱ። እስራኤላውያን በጣም ፈርተው ስለ ነበር ምድማውያን እንዳያገኙአቸው፣ በየሸለቆውና በየዋሻው ይሸሽጉ ነበር። በመጨረሻም እንዲያድናቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።፡

አንድ ቀን፣ ጌዴዎን የሚባል እስራኤላዊ ምድያማውያን ሰብሉን እንዳይወስዱበት ተደብቆ እህል ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ጌዴዎን መጥቶ እንዲህ አለው ‹‹አንተ ብርቱ ተዋጊ ሰው እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው። ሂድና እስራኤልን ከምድያማውያን አድን።››

የጌዴዎን አባት ለጣዖት አምልኮ የተዘጋጀ መሠዊያ ነበረው። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን ያንን መሠዊያ እንዲያፈርስ ተናገረው። ነገር ግን ጌዴዎን ሕዝቡን ስለ ፈራ እስኪመሽ ድረስ ጠበቀ። ከዚያም መሠዊያውን አፈራረሰው፤ እስኪደቅቅ ድረስም ሰባበረው። በአጠገቡም ለእግዚአብሔር ዐዲስ መሠዊያን አዘጋጀ። ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን ሠዋበት።

በማግስቱ ጠዋት ሕዝቡ አንድ ሰው መሠዊያቸውን እንዳፈራረሰው ተመልክተው እጅግ ተበሳጩ። ጌዴዎንን ለመግደል ወደ ጌዴዎን ቤት ሄዱ። ነገር ግን የጌዴዎን አባት ‹‹ለምን አምላካችሁን ለማገዝ ትሞክራላችሁ? እርሱ አምላክ ከሆነ ራሱን ይከላከል!›› አላቸው። ይህንንም ስላለ ሕዝቡ ጌዴዎንን አልገደሉትም።

ምድያማውያን አስራኤላውያንን ለመዝረፍ እንደ ገና መጡ። ቊጥራቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር ማንም ሊቈጥራቸው አይችልም ነበር። ጌዴዎንም ምድያማውያንን ለመውጋት እስራኤላውያንን ጠራ። እግዚአብሔር እርሱን ተጠቅሞ እስራኤልን ያድን እንደ ሆነ ለማረጋገጥ ጌዴዎን ሁለት ምልክቶችን ከእግዚአብሔር ጠየቀ።

የመጀመሪያው ምልክት፦የበግ ፀጉር በምድር ላይ አድርጎ የጠዋቱ ጤዛ በበግ ፀጉር ላይ ብቻ እንጂ በምድር ላይ እንዳይሆን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንደዚያው አደረገ። በሚቀጥለው ምሽት ጌዴዎን እግዚአብሔርን ፤ መሬቱ በጠዋቱ ጤዛ እንዲረጥብ ጨርቁ ግን ደረቅ እንዲሆን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንደዚያው አደረገ። እነዚህ ሁለቱ ምልክቶች እግዚአብሔር እርሱን ተጠቅሞ እስራኤልን ከምድያም እንደሚያድን ለጌዴዎን ማስረጃ ሆኑለት።

32,000 እስራኤላውያን ወታደሮች ወደ ጌዴዎን መጡ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ቊጥራቸው ብዙ ነው አለው። ስለዚህ ጌዴዎን መዋጋት የፈሩትን 22,000 ወታደሮችን ወደ ቤታቸው መለሳቸው። እግዚአብሔር ጌዴዎንን አሁንም የወታደሩ ቊጥር ብዙ ነው አለው። ስለሆነም ጌዴዎን 300 ወታደሮችን አስቀርቶ ሌሎቹን ወደ ቤታቸው መለሳቸው።

በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን ‹‹ወደ ምድያማውያን ጦር ሠፈር ውረድ፣ የሚሉትንም ስትሰማ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ አትፈራቸውም›› አለው። ስለ ሆነም ጌዴዎን ወደ ምድያማውያን ጦር ሠፈር በዚያው ሌሊት ወርዶ አንድ የምድያም ወታደር ለጓደኛው በሕልሙ ያየውን ነገር ሲነገረው ሰማ፤ ጓደኛውም መልሶ “ይህ ሕልም የሚለው የጌድዎን ጦር ምድያማውያንን እንደሚያሸንፍ ነው” አለ። ጌዴዎን ይህን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ።

ከዚያም ጌዴዎን ወደ ወታደሮቹ ተመልሶ ለእያንዳንዳቸው ቀንደ መለከት፣ ማሰሮ እና ችቦ ሰጣቸው።እነሱም የምድያም ሠራዊት ተኝቶ እያለ ሰፍሮ የነበረበትን የጦር ሠፈር ከበቡ። የጌድዎን 300 ወታደሮች ችቦ በማሰሮው ውስጥ ይዘው ስለነበር የምድያም ወታደሮች የችቦውን ብርሃን ማየት አልቻሉም።

ከዚያም የጌዴዎን ወታሮች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜ ማሰሮዎቻቸውን ሰበሩ፤ ወዲያው የችቦው ብርሃን በድንገት አበራ። ቀንደ መለከታቸውን እየነፉ ‹‹የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ›› እያሉ ጮኹ።

እግዚአብሔርም ምድያማውያንን ግራ አጋባቸው፣ እርስ በርሳቸውም ተገዳደሉ። ወዲያው በየቤታቸው ያሉ እስራኤላውያን ምድያማውያንን ለማባረር እንዲረዱ ተጠሩ። ብዙዎችን ምድማውያንን ገደሉ የተቀሩቱንም ከእስራኤል ምድር አባረሩ። በዚያን ቀን 120,000 የምድያም ሰዎች ሞቱ። እግዚአብሔርም እስራኤልን አዳነ።

ሕዝቡም ጌዴዎንን ንጉሣቸው እንዲሆን ፈለጉ። ጌዴዎን ግን ይህን እንዲያደርጉ አልፈቀደላቸውም፤ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ከምድያማውያን የወሰዱአቸውን የወርቅ ቀለበት እንዲያመጡ ጠየቃቸው። ሕዝቡም ለጌዴዎን እጅግ ብዙ ወርቅ ሰጡት።

ጌዴዎንም ወርቁን አቅልጦ ሊቀ ካህኑ እንደሚለብሰው ልዩ ልብስ አድርጎ አሠራው። ነገር ግን ሕዝቡ ያንን ልብስ እንደ ጣዖት ሊያመልኩት ጀመሩ። ከዚያም የተነሣ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸው እንዲያሸንፉአቸው አድርጎ ቀጣቸው። በመጨረሻም ሕዝቡ አሁንም እግዚአብሔር እንዲያድናቸው ጠየቁ፣ እግዚአብሔርም ሌላ አዳኝ ላከላቸው።

እንዲህ ያለው ሁኔታ ብዙ ጊዜ ተደጋገመ። እስራኤላውያን ኃጢአትን ያደርጋሉ፣ እግዚአብሔር ይቀጣቸዋል፣ እንደ ገና ንስሐ ይገባሉ፣ እግዚአብሔርም ያድናቸው ዘንድ አዳኝን ይልክላቸዋል። ለብዙ ዓመታት እግዚአብሔር እስራኤልን ከጠላቶቻቸው ለማዳን ብዙ ነፃ አውጪዎችን ልኮላቸዋል።

በመጨረሻም፣ ሕዝቡ እንደሌሎቹ ሁሉ አሕዛብ ንጉሥን እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ጠየቁ። በጦርነት የሚመራቸው፣ ረጅምና ጠንካራ የሆነ ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ። እግዚአብሔር ግን ይህንን ጥያቄአቸውን አልወደደም፣ ሆኖም እንደ ፈለጉት ንጉሥን ሰጣቸው።
__የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- መሳፍንት 1-5፣ 6-8፡፡
17. እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

ሳኦል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ነበር፡፡ እርሱ ልክ ሕዝቡ እንደ ፈለጉት ረጅምና መልከ መልካም ነበር፡፡ ሳኦል እስራኤልን በገዛባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ጥሩ ንጉሥ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለእግዚአብሔር ያልታዘዘ ክፉ ሰው ሆነ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ቀን በሳኦል ቦታ ንጉሥ የሚሆን የተለየ ሰው መረጠ፡፡

እግዚአብሔር ከሳኦል በኋላ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊት የተባለውን እስራኤላዊ ወጣት መረጠ፡፡ ዳዊት ከቤተ ልሔም ከተማ የሆነ የበጎች እረኛ ነበር፡፡ ዳዊት በተለያዩ ጊዜያት የአባቱን በጎች ሲጠብቅ፣ በጎቹን ለማጥቃት የመጡትን አንበሳና ድብ ገድሎ ነበር፡፡ ዳዊት በእግዚአብሔር የሚያምንና ለእርሱም የሚታዘዝ ትሑትና ጻድቅ ሰው ነበር፡፡

ዳዊት ታላቅ ወታደርና መሪ ሆነ፡፡ ዳዊት ገና ወጣት በነበረ ጊዜ ጎልያድ ተብሎ ከሚጠራ ግዙፍ ሰው ጋር ተዋጋ፡፡ ጎልያድ የሠለጠነ ወታደር፣ በጣም ብርቱ፣ እንዲሁም ቁመቱ ከሞላ ጎደል ሦስት ሜትር ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጎልያድን ገድሎ እስራኤልን እንዲያድን ዳዊትን ረዳው፡፡ ከዚያ በኋላ ዳዊት በሕዝቡ የተመሰገነባቸውን፣ በእስራኤል ጠላቶች ላይ ብዙ ድሎችን አገኘ፡፡

ሳኦል ሕዝቡ ለዳዊት በነበራቸው ፍቅር ቀና፡፡ ሳኦል ብዙ ጊዜ ዳዊትን ሊገድለው ሞከረ፣ ስለዚህ ዳዊት ከሳኦል ተሸሸገ፡፡ አንድ ቀን ሳኦል ይገድለው ዘንድ ዳዊትን እየፈለገው ነበር፡፡ ሳኦል ዳዊት ከእርሱ ተሸሽጎበት ወደ ነበረው ዋሻ ሄደ፣ ነገር ግን ሳኦል አላየውም ነበር፡፡ ዳዊትም ወደ ሳኦል በጣም ተጠግቶ ነበርና ሊገድለው ይችል ነበር፣ ነገር ግን አልገደለውም፡፡ በዚህ ፈንታ ዳዊት ንጉሥ ለመሆን እንዳልገደለው ለሳኦል ለማረጋገጥ የሳኦልን ልብስ ዘርፍ ቈረጠ፡፡

በመጨረሻ፣ ሳኦል በጦርነት ሞተ፣ ዳዊትም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ ዳዊት ጥሩ ንጉሥ ነበረ፣ ሕዝቡም ወደዱት፡፡ እግዚአብሔር ዳዊትን ባረከው፣ ስኬታማም አደረገው፡፡ ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን ተዋጋ፣ የእስራኤልን ጠላቶች እንዲያሸንፍም እግዚአብሔር ረዳው፡፡ ዳዊት ኢየሩሳሌምን አሸንፎ ያዘና ዋና ከተማው አደረጋት፡፡ በዳዊት ንግሥና ጊዜ፣ እስራኤል ኃያልና ባለ ጠጋ ሆነች፡፡

ዳዊት እስራኤላውያን ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትና ለእርሱ መሥዋዕቶችን የሚያቀርቡበት ቤተ መቅደስ ለመሥራት ፈለገ፡፡ ሕዝቡ ለ400 ዓመት ገደማ ሙሴ በሠራው የመገናኛ ድንኳን እግዚአብሔርን ያመልኩና መሥዋዕቶችን ያቀርቡለት ነበር፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ የሚል መልዕክት በነቢዩ ናታን በኩል ወደ ዳዊት ላከው፣ ‹‹አንተ የጦርነት ሰው ስለ ሆንክ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ አትሠራልኝም፡፡ ልጅህ ይሠራዋል፡፡ ነገር ግን አንተን በእጅጉ እባርክሃለሁ፡፡ ከዝርያዎችህ አንዱ በሕዝቤ ላይ ንጉሥ ሆኖ ለዘላለም ይገዛል!›› ለዘላለም የሚገዛው ብቸኛው የዳዊት ዝርያ፣ መሲሑ ነው፡፡ መሲሑ የዓለምን ሕዝቦች ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ምርጥ ነው፡፡

ዳዊት እነዚህን ቃሎች በሰማ ጊዜ፣ ይህንን ታላቅ ክብርና ብዙ በረከቶችን ሊሰጠው ቃል ስለ ገባለት ወዲያውኑ እግዚአብሔርን አመሰገነ አወደሰም፡፡ ዳዊት እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች መቼ እንደሚያደርግ ግን አላወቀም፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን መሲሑ እስከሚመጣ ረዘም ላለ ጊዜ፣ ከሞላ ጐደል 1000 ዓመታት መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

ዳዊት በፍትሕና በታማኝነት ለብዙ ዓመታት ገዛ፣ እግዚአብሔርም ባረከው። ይሁን እንጂ፣ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ በእግዚአብሔር ላይ ክፉኛ ኃጢአት ሠራ።

አንድ ቀን የዳዊት ወታደሮች በሙሉ ከቤታቸው ርቀው ጦርነት በሚዋጉበት ጊዜ፣ እርሱ ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ ዐየ። ስምዋ ቤርሳቤህ ነበር።

ዳዊት ፊቱን ከሷ በማዞር ፈንታ፣ ወደ እርሱ እንዲያመጣት ሰው ላከ፡፡ ከእርስዋ ጋር ተኛና ወደ ቤቷ መልሶ ላካት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤርሳቤህ አርግዣለሁ ብላ ወደ ዳዊት መልእክት ላከች፡፡

ኦርዮ ተብሎ የሚጠራው የቤርሳቤህ ባል ከዳዊት ምርጥ ወታደሮች አንዱ ነበር፡፡ ዳዊት ኦርዮን ከጦርነቱ ቦታ ጠራውና ከሚስቱ ጋር እንዲሆን ነገረው፡፡ ነገር ግን ኦርዮ የቀሩት ወታደሮች በጦርነት ላይ እያሉ ወደ ቤት አልሄድም አለ፡፡ ስለዚህ ዳዊት ኦርዮንን ወደ ጦርነቱ መልሶ ላከውና ይገደል ዘንድ ጠላት እጅግ በበረታበት ቦታ እንዲያሰልፈው ለሠራዊቱ ዋና አዛዥ ነገረው፡፡

ኦርዮ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት፡፡ በኋላ እርስዋ ለዳዊት ወንድ ልጅን ወለደችለት፡፡ እግዚአብሔር ዳዊት ስላደረገው ነገር በጣም ተቈጣ፣ ኃጢአቱ እንዴት ክፉ እንደ ነበረ ለዳዊት እንዲነግረውም እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ላከው፡፡ ዳዊት ኃጢአቱን ተናዘዘና እግዚአብሔር ይቅር አለው፡፡ ዳዊት በቀረው የሕይወቱ ዘመን በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳ፣ እግዚአብሔርን ተከተለ፤ ታዘዘውም፡፡

ነገር ግን ዳዊት ለሠራው ኃጢአት ቅጣት እንዲሆን ሆኖ የተወለደው ልጁ ሞተበት፡፡ ደግሞም በቀረው የሕይወቱ ዘመን በዳዊት ቤተ ሰብ ውጊያ ነበረ፣ የዳዊት ኃይልም በእጅጉ ተዳከመ፡፡ ዳዊት ለእግዚአብሔር ያልታመነ ቢሆንም እንኳ፣ እግዚአብሔር አሁንም ለተስፋዎቹ የታመነ ነበረ፡፡ በኋላ ዳዊትና ቤርሳቤህ ሌላ ወንድ ልጅ ወለዱ፣ ስሙንም ሰሎሞን አሉት፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ሳሙኤል 10፡15-19፤ 24፤ 31፤ 2ኛ ሳሙኤል 5፤ 7፤ 11-12፡፡
18. ለሁለት የተከፈለው መንግሥት

ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ ዳዊት ሞተ፣ ልጁ ሰሎሞንም እስራኤልን ይገዛ ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተናገረውና ከሁሉ በላይ ምን እንደሚፈልግ ጠየቀው፡፡ ሰሎሞን ጥበብን እንዲሰጠው በለመነ ጊዜ፣እግዚዘብሔር ደስ አለውና በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ በላይ እጅግ በጣም ጠቢብ ሰው አደረገው፡፡ ሰሎሞን ብዙ ነገሮችን የሚያውቅ በጣም ጠቢብ ፈራጅ ሆነ፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር በጣም ባለ ጠጋ አደረገው፡፡

ሰሎሞን በኢየሩሳሌም አባቱ ዳዊት ሊሠራ ያቀደውንና ለግንባታው የሚያስፈልጉ ነገሮች የሰበሰበለትን ቤተ መቅደስ ሠራ፡፡ አሁን ሕዝቡ በመገናኛው ድንኳ ፈንታ በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን አመለኩ መሥዋዕትንም አቀረቡለት፡፡ እግዚአብሔር መጥቶ በቤተ መቅደሱ ሆነ፣ በዚያም ከሕዝቡ ጋር ኖረ፡፡

ነገር ግን ሰሎሞን የሌሎች አገሮች ዜጎች የሆኑ ሴቶችን ወደደ። ከሞላ ጐደል 1000 የሚሆኑ ብዙ ሴቶችን በማግባት ለእግዚአብሔር አልታዘዘም! ከእነዚህ ሴቶች ብዙዎቹ ከሌላ አገሮች የመጡ ነበሩ፣ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን አምጥተው ማምለካቸውን ቀጠሉ። ሰሎሞንም በሸመገለ ጊዜ፣ እርሱም ደግሞ የእነርሱን አማልክት አመለከ።

እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ተቈጣ፣ ሰሎሞን ባለመታመኑ እንደ መቀጣጫ እንዲሆን ከእርሱ ሞት በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ሁለት መንግሥታት እንደሚከፍል ተናገረ።

ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ልጁ ሮብዓም ነገሠ፡፡ ሮብዓም ሞኝ ነበረ፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ንጉሥነቱን ሊያጸድቁለት ተሰብስበው መጡ፡፡ ሰሎሞን ብዙ ከባድ ሥራ እንዳሠራቸውና ብዙ ግብር እንዳስከፈላቸው ለሮብዓም ቅሬታቸውን ተናገሩ፡፡

ሮብዓም በሞኝነት እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ ‹‹አባቴ ሰሎሞን ከባድ ሥራ አሠርቶናል ብላችሁ ዐስባችኋል፣ ነገር ግን እኔ ከእርሱ የባሰ ከባድ ሥራ አሠራችኋለሁ፣ ከእርሱ የባሰም በኃይል እቀጣችኋለሁ፡፡››

ስለዚህ ዐሥሩ የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች በሮብዓም ላይ ዓመፁ፡፡ ሁለት ነገዶች ብቻ ለእርሱ ባላቸው ታማኝነት ቀጠሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ነገዶች የይሁዳ መንግሥት ሆኑ፡፡

በሮብዓም ላይ ያመፁት ሌሎቹ ዐሥር የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ኢዮርብዓም የተባለውን ሰው ንጉሣቸው አድርገው ሾሙት፡፡ በምድሪቱ ሰሜናዊ ክፍል መንግሥታቸውን አቋቋሙ፤ የእስራኤል መንግሥት ተብለውም ተጠሩ፡፡

ኢዮርብዓም በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀና ሕዝቡ ኃጢአት እንዲሠሩ አደረገ፡፡ በይሁዳ መንግሥት ባለው ቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን በማምለክ ፈንታ ሕዝቡ ያመልኩአቸው ዘንድ ሁለት ጣዖታትን ሠራላቸው፡፡

የይሁዳና የእስራኤል መንግሥታት ጠላቶች ሆኑና ብዙ ጊዜ እርስ በርስ ተዋጉ።

በዐዲሲቱ የእስራኤል መንግሥት የነገሡት ነገሥታቱ ሁሉ ክፉዎች ነበሩ። ከእነዚህ ነገሥታት አብዛኞቹ፣ በእነርሱ ቦታ መንገሥ በፈለጉ ሌሎች እስራኤላውያን ተገደሉ።

ነገሥታቱ ሁሉና አብዛኞቹ የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ ጣዖትን አመለኩ፡፡ የጣዖት አምልኮአቸው ብዙውን ጊዜ ግብረ ገብነት የጐደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነትና አንዳንድ ጊዜ እንደውም ልጆችን መሠዋትንም ያካተተ ነበር፡፡

የይሁዳ ነገሥታት የዳዊት ዝርያዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ነገሥታት አንዳንዶቹ በቅንነት የገዙና እግዚአብሔርን ያመለኩ ጥሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የይሁዳ ነገሥታት ክፉዎችና ብልሹዎች ነበሩ፣ ጣዖታትንም ያመልኩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ነገሥታት ልጆቻቸውን እንኳ ለሐሰት አማልክት ሠውተዋል፡፡ ደግሞም አብዛኞቹ የይሁዳ ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ፤ ሌሎች አማልክትንም አመለኩ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ነገሥት 1-6፤ 11-12፡፡
19. ነቢያቱ

እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ታሪክ በሙሉ ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፡፡ ነቢያቱም መልእክትን ከእግዚአብሔር ሰምተው ለሕዝቡ ይነግሩ ነበር፡፡

አክአብ በእስራኤል መንግሥት ላይ በነገሠ ጊዜ ኤልያስ ነቢይ ነበረ፡፡ አክዓብ በኣል ተብሎ የሚጠራ የሐሰት አምላክ እንዲያመልኩ ሕዝቡን ያደፋፈረ ክፉ ሰው ነበር፡፡ ኤልያስ ለአክዓብ፣ ‹‹እኔ እንዲዘንብ እስከምናገር ድረስ በእስራኤል ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም›› አለው፡፡ ይህ አክዓብን በጣም አስቈጣው፡፡

አክዓብ ኤልያስን ሊገድለው ይፈልግ ስለ ነበር እግዚአብሔር ኤልያስን ይሸሸግ ዘንድ በምድረ በዳ ወዳለ ምንጭ እንዲሄድ ነገረው። በየጠዋቱና በየምሽቱ ወፎች እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር። አክዓብና ጦር ሠራዊቱ ኤልያስን ፈለጉት፣ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም። ድርቁ በጣም ከባድ ስለነበር በመጨረሻ ምንጩ ደረቀ።

ስለዚህ ኤልያስ ወደ አንድ ጐረቤት አገር ሄደ። በዚያችም አገር በድርቁ ምክንያት ረሃብ ስለነበር አንዲት መበለትና ወንድ ልጅዋ ምግብ ሊያልቅባቸው ተቃርበው ነበር። ነገር ግን ኤልያስን ተንከባከቡት፣ ስለሆነም እግዚአብሔር ዱቄቱ ከማድጋ ዘይቱም ከማሰሮ እንዳይጐድል አድርጎ መገባቸው። በረሀቡ ጊዜ ሁሉ ምግብ ነበራቸው። ኤልያስ በዚያ ለረዥም ጊዜ ተቀመጠ።

ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ኤልያስ ወደ እስራኤል መንግሥት ተመልሶ ዝናብ እንደሚዘንብ ለአክዓብ እንዲነግረው እግዚአብሔር ለኤልያስ ነገረው። አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜ፣ ‹‹አንተ ችግር ፈጣሪ፣ አለህ እንዴ!›› አለው። ኤልያስ እንዲህ ብሎ መለሰት፣ ‹‹ችግር ፈጣሪ አንተ ነህ እንጂ እኔ አይደለሁም! እውነተኛውን አምላክ፣ ያህዌን ትተህ፣ በኣልን አምልከሃል፤ የእስራኤልን መንግሥት ሕዝብ ሁሉ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰብስብ።››

450ዎቹ የበኣል ነቢያትን ጨምሮ የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጡ፡፡ ኤልያስም ለሕዝቡ፣ ‹‹ስንት ጊዜ ዐሳባችሁን ትለውጣላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ከሆን እርሱን አገልግሉ! በኣል አምላክ ከሆን እርሱን አገልግሉ!›› አላቸው፡፡

ከዚያም ኤልያስ ለበኣል ነቢያት፣ ‹‹አንድ ወይፈን እረዱና መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡት፣ ነገር ግን እሳት አታንድዱ፡፡ እኔም እንደዚሁ አደርጋለሁ፡፡ በእሳት የሚመልስ አምላክ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው›› አላቸው፡፡ ስለዚህ የበኣል ካህናት መሥዋዕት አዘጋጁ፤ ነገር ግን እሳት አላነደዱም፡፡

ከዚያ በኋላ የበኣል ነቢያት ‹‹በኣል ሆይ፣ ስማን!›› ብለው ወደ በኣል ጸለዩ። ቀኑን ሙሉ ጸለዩ፣ ጮኹ፣ እንዲሁም ሰውነታቸውን በቢላዋ ቈረጡ፣ ነገር ግን መልስ አልነበረም።

በቀኑ መጨረሻ፣ ኤልያስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጀ፡፡ ከዚያም ሥጋው፣ እንጨቱ፣ እንዲሁም በመሠዊያው ዙሪያ ያለው መሬት እንኳ ሳይቀር ፍጹም እስኪረጥብ ድረስ ዐሥራ ሁለት ጋን ሙሉ ውሃ በመሥዋዕቱ ላይ እንዲያፈሱ ለሕዝብ ነገራቸው፡፡

ከዚያም ኤልያስ እንዲህ ብሎ ጸለየ፣ ‹‹ያህዌ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ እንደ ሆንክና እኔም አገልጋይህ እንደ ሆንኩ ዛሬ ዐሳየን። አንተ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆንክ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ መልስልኝ›› አለ።

ወዲያውኑ፣ እሳት ከሰማይ ወደቀና ሥጋውን፣ እንጨቱን፣ ድንጋዩን፣ ቈሻሻውን፣ እንዲሁም በመሠዊያው ዙሪያ የነበረውን ውሃ እንኳ ሳይቀር አቃጠለ፡፡ ሕዝቡ ይህን ባዩ ጊዜ መሬት ላይ ወደቁና ‹‹ያህዌ አምላክ ነው! ያህዌ አምላክ ነው!›› አሉ፡፡

ከዚያም ኤልያስ፣ ‹‹ከበኣል ነቢያት አንድም እንዳያመልጥ!›› አለ። ስለዚህ ሕዝቡ የበኣልን ነቢያት ያዙና ወስደው ገደሉአቸው።

ከዚያ በኋላ ኤልያስ ለንጉሥ አክዓብ፣ ‹‹ዝናብ መጥቶአልና ፈጥነህ ወደ ከተማ ተመለስ›› አለው፡፡ ወዲያውኑ ሰማዩ ጠቈረ፣ ከባድ ዝናብም መዝነብ ጀመረ፡፡ ያህዌ ድርቁን አቆመው፤ እውተኛ አምላክ መሆኑንም አረጋገጠ፡፡

ከኤልያስ ዘመን በኋላ፣ እግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን ኤልሳዕ የተባለ ሰውን መረጠ። እግዚአብሔር በኤልሳዕ በኩል ብዙ ተአምራትን አደረገ። ከተአምራቱ አንዱ አስከፊ የቆዳ በሽታ በያዘው የጠላት ጦር ሠራዊት አዛዥ በነበረው ንዕማን ላይ ተከሠተ። ስለ ኤልሳዕ ሰምቶ ነበርና ስለዚህ እንዲፈውሰው ኤልሳዕን ሄዶ ጠየቀው። ኤልሳዕ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንዲል ለንዕማን ነገረው።

በመጀመሪያ ንዕማን ተቈጣና ሞኝነት ስለ መሰለው ኤልሳዕ የነገረውን ነገር አላደረገውም። በኋላ ግን ዐሳቡን ለወጠና በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ። በመጨረሻ ከውሃው በወጣ ጊዜ ቆዳው ፍጹም ተፈወሰ! እግዚአብሔር ፈወሰው።

እግዚአብሔር ሌሎች ብዙ ነቢያትን ላከ፡፡ ሁላቸውም ለሕዝቡ ጣዖታትን ማምለክ እንዲያቆሙና ለሌሎች ፍትሕንና ምሕረትን ማሳየት እንዲጀምሩ ነገሩአቸው፡፡ ነቢያቱ ሕዝቡ ክፉ መሥራትን ባያቆሙና ለእግዚአብሔር መታዘዝ ባይጀምሩ፣ እግዚአብሔር በበደለኝነት እንደሚፈርድባቸውና፣ እንደሚቀጣቸውም አስጠነቀቁአቸው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር አልታዘዙም። ብዙውን ጊዜ ለነቢያት የነበራቸው አያያዝ መጥፎ ነበረ፣ አንዳንድ ጊዜ እንዳውም ይገድሉአቸው ነበር። በአንድ ወቅት፣ ነቢዩ ኤርምያስ ደረቅ በሆነ የውሃ ጕድጓድ ውስጥ ተጥሎ በዚያ እንዲሞት ተትቶ ነበር። በጕድጓዱ መጨረሻ በነበረው ጭቃ ውስጥ እየሰመጠ ነበር፣ ነገር ግን ንጉሡ ራራለትና ከመሞቱ በፊት ከጕድጓዱ ጐትተው እንዲያወጡት አገልጋዮቹን አዘዛቸው።

ነቢያቱ ሕዝቡ ቢጡሉአቸውም እንኳ ስለ እግዚአብሔር መናራቸውን ቀጠሉ፡፡ ንስሐ ባይገቡ እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው ሕዝቡን አስጠነቀቁአቸው፡፡ ደግሞም የእግዚአብሔር መሲሕ እንደሚመጣ ስለተሰጠው ተስፋ ሕዝቡን አስታወቋቸው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ነገሥት 16-18፤ 2ኛ ነገሥት 5፤ ኤርምያስ 38፡፡
20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ

የእስራኤል መንግሥትና የይሁዳ መንግሥት ሁለቱም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ፡፡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር በሲና ተራራ ያደረገውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፡፡ እግዚአብሔርም ንስሐ እንዲገቡና እንደገና እንዲያመልኩት ሊያስጠነቅቃቸው ነቢያቱን ላከ፣ እነርሱ ግን አንታዘዝም አሉ፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸው እንዲያጠፉአቸው በመፍቀድ ሁለቱንም መንግሥታት ቀጣቸው። ኃያልና ጨካኝ የሆነው የአሦር ንጉሠ ነገሥት ግዛት የእስራኤልን መንግሥት ደመሰሰው፣ ብዙ የእስራኤል መንግስት ሕዝብንም አዘርያውያን ገደሉ። ንብረቶቻቸውንም ሁሉ ወሰዱ፣ ከአገሪቱ አብዛኛውንም አቃጠሉ።

አሦርያውያንም መሪዎችን፣ ሀብታሞችን፣ እንዲሁም ሙያ የነበራቸውን ሰዎች ሁሉ ሰበሰቡና ወደ አሦር ወሰዱአቸው፡፡ ያልተገደሉት በጣም ድሆች የነበሩት እስራኤላውያን ብቻ በእስራኤል መንግሥት ቀሩ፡፡

ከዚያም አሦራውያን የእስራኤል መንግሥት በነበረባት ምድር እንዲኖሩ ባዕዳንን አመጡ፡፡ ባዕዳኑም የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠሩና በዚያ ቀርተው የነበሩትን እስራኤላውያን አገቡ፡፡ ባዕዳንን ያገቡት የእስራኤላውያን ዝርያዎች ሳምራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡

የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ እግዚአብሔርን ስላላመኑበትና ስላልታዘዙት እንዴት እንደ ቀጣቸው በይሁዳ መንግሥት የነበሩት ሕዝብ ዐዩ። እንደዚያም ሆኖ ግን የይሁዳ መንግሥት ሕዝብ የከነዓናውያንን አማልክት ጨምሮ ጣዖታትን አመለኩ። እግዚአብሔርም እንዲያስጠነቅቁአቸው ነቢያትን ላከ፣ እነርሱ ግን አንሰማም አሉ።

አሦራውያን የእስራኤልን መንግሥት ካጠፉ ከ100 ዓመታት ገደማ በኋላ የይሁዳን መንግሥት እንዲወጉ እግዚአብሔር የባቢሎናውያንን ንጉሥ ናቡከደናፆርን ላከ፡፡ ባቢሎን ኃያል የንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበረች፡፡ የይሁዳ ንጉሥም የናቡከደነፆር አገልጋይ ለመሆንና በያመቱ ብዙ ገንዘብ ሊከፍለው ተስማሙ፡፡

ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ በባቢሎን ላይ ዓመፀ፡፡ ስለዚህ ባቢሎናውያን ተመልሰው መጥተው የይሁዳን መንግሥት ወጉ፡፡ የኢየሩሳሌምን ከተማ ያዙ፣ ቤተ መቅደሱን አጠፉ፣ እንዲሁም የከተማይቱንና የቤተ መቅደሱን ንብረት ሁሉ ወሰዱ፡፡

የይሁዳ ንጉሥ ስላመፀበት ሊቀጡ የናቡከደነፆር ወታደሮች የይሁዳን ንጉሥ ወንድ ልጆች በፊቱ ገደሉ፤ እርሱንም ዓይኖቹን አሳወሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በባቢሎን በእስር ቤት እንዲሞት ንጉሡን ወሰዱት፡፡

ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በእርሻ እንዲሠሩ እጅግ በጣም ድሆች የሆኑትን ሰዎች ብቻ በመተው ከሞላ ጐደል የይሁዳን መንግሥት ሕዝብ ሁሉ ወደ ባቢሎን ማርከው ወሰዱ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተስፋዪቱን ምድር እንዲለቁ የተገደዱበት ይህ ወቅት የባቢሎን ምርኮ ተብሎ ይጠራል፡፡

ምንም እንኳ እግዚአብሔር ወደ ምርኮ በመውሰድ ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ቢቀጣቸውም እነርሱንና ተስፋዎቹን አልረሳም። እግዚአብሔር ሕዝቡን መጠበቁንና በነቢያቱ በኩል እነርሱን ማነጋገሩን ቀጠለ። ከሰባ ዓመት በኋላ፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደ ገና እንዲመለሱ ተስፋ ሰጠ።

ከሰባ ዓመታት ገደማ በኋላ፣ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎንን አሸነፈ፣ ስለዚህ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት የባቢሎንን ንጉሠ ነገሥት ግዛት ተካ፡፡ በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን አይሁዶች ተብለው ይጠሩ ነበር። አብዛኞቻቸውም ሕይወታቸውን በሙሉ በባቢሎን የኖሩ ነበሩ፡፡ በጣም ያረጁ ጥቂት አይሁዶች ብቻ የይሁዳን ምድር አስታወሱ፡፡

የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ኃይለኛ ቢሆንም ለማረካቸው ሕዝብ መሐሪ ነበር፡፡ ቂሮስ የፋርሳውያን ንጉሥ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ወደ ይሁዳ መመለስ የፈለገ ማንኛውም አይሁዳዊ ፋርስን ለቆ ወደ ይሁዳ መመለስ እንደሚችል ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲሠሩም የገንዘብ ድጋፍ ሳይቀር አደረገላቸው! ስለዚህ በምርኮ ከቆዩባቸው ሰባ ዓመታት በኋላ፣ ጥቂት የአይሁዶች ቡድን በይሁዳ ወዳለችው ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሱ፡፡

ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ መቅደሱንና በከተማዪቱ ዙሪያ ያለውን ቅጥር እንደገና ሠሩ። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በሌሎች ሕዝቦች የተገዙ ቢሆኑም፣ ዳግመኛ በተስፋዪቱ ምድር ኖሩና በቤተ መቅደሱ እግዚአብሔርን አመለኩ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ2ኛ ነገሥት 17፤ 24-25፤ 2ኛ ዜና 36፤ ዕዝራ 1-10፤ ነህምያ 1-13፡፡
21. እግዚአብሔር ስለ መሲሑ ተስፋ ሰጠ

ገና ከመጀመሪያው፣ እግዚአብሔር መሲሑን ለመላክ ዐቀደ፡፡ የመጀመሪያው የመሲሑ ተስፋ ወደ አዳምና ሔዋን መጣ፡፡ እግዚአብሔር የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጥ የሔዋን ዘር እንደሚወለድ ተስፋ ሰጠ፡፡ ሔዋንን ያታለለው እባብ ሰይጣን ነበር፡፡ ተስፋው መሲሑ ሰይጣንን ፍጹም ያሸንፈዋል የሚል ነው፡፡

በእርሱ በኩል የዓለም ሕዝብ ወገኖች ሁሉ በረከት እንደሚቀበሉ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ ሰጠው፡፡ ይህ በረከት ወደ ፊት መሲሑ ሲመጣ ይፈጸማል፡፡ እርሱ በዓለም ካሉ ከሁሉም የሕዝብ ወገኖች የሆኑ ሕዝቦች እንዲድኑ ያደርጋል፡፡

ወደ ፊት እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እንደሚያስነሣ እግዚአብሔር ለሙሴ ተስፋ ሰጠው፡፡ ይህ ቆይቶ ስለሚመጣው መሲሕ የተሰጠ ሌላ ተስፋ ነበር፡፡

ከዝርያዎቹ አንዱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ንጉሥ ሆኖ ለዘላለም እንደሚገዛ እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት ተስፋ ሰጠው፡፡ ይህም መሲሑ ከዳዊት ዝርያዎች አንዱ ይሆናል ማለት ነበር፡፡

እግዚአብሔር ዐዲስ ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ተስፋ ሰጠ፣ ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር በሲና ከእስራኤል ጋር እንዳደረገው ቃል ኪዳን ግን አይደለም፡፡ በዐዲሱ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ሕጉን በሕዝቡ ልብ ይጽፋል፣ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በግል ያውቁታል፣ ሕዝቡም ይሆናሉ፣ እግዚአብሔርም ኃጢአታቸውን ይቅር ይላል፡፡ መሲሑ ዐዲሱን ኪዳን ይጀምራል፡፡

ደግሞም የእግዚአብሔር ነቢያት መሲሑ ነቢይም፣ ካህንም እንዲሁም ንጉሥም ይሆናል አሉ፡፡ ነቢይ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ የሚያውጅ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ለመላክ ተስፋ የሰጠው መሲሕ እንከን የሌለው ነቢይ ይሆናል፡፡

የእስራኤላውያን ካህናት ስለ ሕዝብ ኃጢአት ለሚደርስባቸው ቅጣት ምትክ እንዲሆን በሕዝብ ፈንታ ለእግዚአብሔር መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡ ደግሞም ካህናት ስለ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ይጸለዩ ነበር፡፡ መሲሑ ደግሞ ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ፍጹም ሊቀ ካህናት ይሆናል፡፡

ንጉሥ ማለት በመንግሥቱ ላይ የሚገዛና በሕዝቡ ላይ የሚፈርድ ሰው ነው። እንዲሁም መሲሑ በቅድመ አያቱ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ፍጹም ንጉሥ ይሆናል። በመላው ዓለም ላይ ለዘላለም ይገዛል፣ እንዲሁም ሁልጊዜ በቅንነት ይፈርዳል፤ ትክክለኛ ውሳኔም ይሰጣል።

የእግዚአብሔር ነቢያት ስለ መሲሑ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ተንብየዋል፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ መሲሑ ከመምጣቱ በፊት ታላቅ ነቢይ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተነበየ፡፡ መሲሑ ከአንዲት ድንግል እንደሚወለድ ነቢዩ ኢሳይያስ ተነበየ፡፡ ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በቤተልሔም ከተማ ይወለዳል አለ፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ መሲሑ በገሊላ ይኖራል፣ ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን ያጽናናል፣ እንዲሁም ለተማረኩት ነጻነትንና ለታሰሩት መፈታትን ያውጃል ብሎአል፡፡ ደግሞም ነቢዩ መሲሑ የታመሙና መስማት፣ ማየት፣ መናገር፣ ወይም መራመድ የማይችሉትን ሕዝብ እንደሚፈውስ ተነበየ፡፡

ደግሞም ነቢዩ ኢሳይያስ ሰዎች ያለ ምክንያት መሲሑን እንደሚጠሉትና እንደማይቀበሉት ተነበየ። ሌሎች ነቢያት መሲሑን የገደሉት እነዚያ በልብሶቹ ላይ ዕጣ እንድሚጣጣሉና ወዳጁ አሳልፎ እንደሚሰጠው አስቀድመው ተነበዩ። ነቢዩ ዘካርያስ መሲሑን አሳልፎ የሚሰጠው ወዳጅ ሠላሳ ብር እንደሚከፈለው ተነበየ።

ደግሞም ነቢያት ስለ መሲሑ አሟሟት ተናገሩ፡፡ ኢሳይያስ ሰዎች በመሲሑ እንደሚተፉበት፣ እንደሚያፌዙበትና እንደሚመቱት ተነበየ፡፡ ምንም ክፉ ነገር ያላደረገ ቢሆንም እንኳ ይወጉታል፤ በታላቅ መከራና ሥቃይ ይሞታል፡፡

ደግሞም ነቢያት መሲሑ ምንም ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ይሆናል ብለዋል፡፡ የሌሎች ሰዎችን የኃጢአት ቅጣት ለመቀበል እርሱ ይሞታል፡፡ የእርሱ መቀጣት በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ሰላምን ያመጣል፡፡ በዚህ ምክንያት መሲሑን ማድቀቅ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፡፡

መሲሑ እንደሚሞትና እግዚአብሔር ደግሞ ከሙታን እንደሚያስነሣው ነቢያት አስቀድመው ተነበዩ፡፡ እግዚአብሔር በመሲሑ ሞትና ትንሣኤ በኩል ኃጢአተኞችን ለማዳንና ዐዲሱን ኪዳን ለመጀመር የያዘውን ዕቅዱን ይፈጽማል፡፡

እግዚአብሔር ለነቢያት ስለ መሲሑ ብዙ ነገሮችን ገለጠላቸው፣ ነገር ግን መሲሑ ከእነዚያ ነቢያት በአንዳቸውም ዘመን አልመጣም። ከእነዚህ ትንቢቶች የመጨረሻው ከተተነበየ ከ400 ዓመታት በኋላ፣ ልክ በትክክለኛው ጊዜ፣ እግዚአብሔር መሲሑን ወደ ዓለም ላከ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 3፡15፤ 12፡1-3፤ ዘዳግም 18፡15፤ 2ኛ ሳሙኤል 7፤ ኤርምያስ 31፤ ኢሳይያስ 59፡16፤ ዳንኤል 7፤ ሚልክያስ 4፡5፤ ኢሳይያስ 7፡14፤ ሚክያስ 5፡2፤ ኢሳይያስ 9፡1-7፤ 35፡3-5፤ 61፡53፤ መዝሙር 22፡18፤ 35፡19፤ 69፡4፤ 41፡9፤ ዘካርያስ 11፡12-13፤ ኢሳይያስ 50፡6፤ መዝሙር 16፡10-11፡፡
22. የዮሐንስ መወለድ

አስቀድሞ እግዚአብሔር በመላእክቱና በነቢያቱ በኩል ለሕዝቡ ተናግሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኃላ ለእነርሱ ሳይነገራቸው 400 ዓመታት አለፉ፡፡ አንድ ቀን በድንገት አንድ መልአክ ዘካርያስ ተብሎ ወደሚጠራ ሽማግሌ ካህን ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ይዞ መጣ፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ፣ ነገር ግን እርስዋ ልጆችን አልወለደችም ነበር፡፡

መልአኩ ዘካርያስን አለው፣ ‹‹ሚስትህ ወንድ ልጅ ትወልዳለች።ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ተጠራዋለህ፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፣ ሕዝቡንም ለመሲሑ ያዘጋጃል!›› ዘካርያስ፣ ‹‹ሚስቴና እኔ ልጆችን ለመውለድ በጣም አርጅተናል! ይህ እንደሚሆን እንዴት ዐውቃለሁ?›› ብሎ መለሰ።

መልአኩ ለዘካርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ “ይህን የምሥራች እንዳመጣላችሁ እግዚአብሔር ላከኝ፡፡ አንተ ስላላመንከኝ፣ ልጁ እስኪወለድ ድረስ መናገር አትችልም፡፡” ወዲያውኑ ዘካርያስ መናገር አልቻለም፡፡ ከዚያ በኋላ መልአኩ ከዘካርያስ ተለየ፡፡ ዘካርያስም ወደ ቤት ተመለሰ፤ ሚስቱም ፀነሰች፡፡

ኤልሳቤጥ የስድስት ወር ነፍሰ ጡር በነበረች ጊዜ፣ ያው መልአክ በድንገት ስምዋ ማርያም ለተባለ ለኤልሳቤጥ ዘመድ ተገለጠ። እርስዋ ድንግል ነበረችና ልታገባ ዮሴፍ ለተባለ ሰው ታጭታ ነበር። መልአኩ፣ ‹‹ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ ለዘላለምም ገዥ ይሆናል›› አለ።

ማርያም‹‹እኔ ድንግል ስለ ሆንኩ፣ ይህ እንዴት ይሆናል?›› ብላ መለሰች። መልአኩ እንዲህ ብሎ አብራራ፣ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል፣ የልዑል እግዚዘብሔር ኃይል ይጸልልሻል። ስለዚህ ልጁ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል።›› ማርያምም አመነች፤ መልአኩ ያለውንም ተቀበለች።

መልአኩ ለማርያም ከተናገረ በኋላ ወዲያወኑ ሄደችና ኤልሳቤጥን ጐበኘቻት። ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ እንደ ሰማች፣ የኤልሳቤጥ ልጅ በሆዷ ውስጥ ዘለለ። ሴቶቹ እግዚአብሔር ስላደረገላቸው ነገር አብረው ሐሤት አደረጉ። ማርያም ኤልሳቤጥን ለሦስት ወራት ከጐበኘቻት በኋላ፣ ወደ ቤትዋ ተመለሰች።

ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅዋን ከወለደች በኋላ፣ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ መልአኩ እንዳዘዘው ሕፃኑን ዮሐንስ ብለው ሰየሙት፡፡ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ዘካርያስ እንደ ገና እንዲናገር ፈቀደለት፡፡ ዘካርያስ እንዲህ አለ፣ ‹‹ሕዝቡን ዐስቦአልና እግዚአብሔር ይመስገን! አንተም ልጄ፣ ለኃጢአታቸው ይቅርታ መቀበል እንዴት እንደሚችሉ ለሕዝቡ የምትናገር የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ!››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 1፡፡
23. የኢየሱስ ልደት

ማርያም ዮሴፍ ለተባለ ጻድቅ ሰው ታጭታ ነበር። እጮኛዋ ዮሴፍ ማርያም መፀነስዋን በሰማ ጊዜ፣ ሕፃኑ የእርሱ እንዳልሆነ ዐወቀ። ስለዚህ ማርያምን ለማሳፈር ስላልፈለገ፣ዝም ብሎ ሊተዋት ዐሰበ። ያንን ከማድረጉ በፊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣና በሕልም ተናገረው።

መልአኩ እንዲህ አለ፡- “ዮሴፍ፣ እጮኛህን ማርያምን ሚስትህ አድርገህ ለመውሰድ አትፍራ። በውስጥዋ ያለው ሕፃን ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ስሙን ኢየሱስ ብለህ ጥራው (ትርጕሙም፣ ያሕዌ ያድናል ማለት ነው)፣ ምክንያቱም ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና።”

ስለዚህ ዮሴፍ ማርያምን ወሰዳት፣ ነገር ግን እስክትወልድ ድረስ ከእርስዋ ጋር አልተኛም፡፡

ማርያም የምትወልድበት ጊዜ እንደ ደረሰ፣ የሮማ መንግሥት ሁሉም ሰው ለቈጠራ ቅድመ አያቶቹ ወደ ኖሩበት ከተማ እንዲሄድ ተናገረ። ዮሴፍና ማርያም ከሚኖሩበት ከናዝሬት ወደ ቤትልሔም ረጅም ጕዞ ተጓዙ፤ ምክንያቱም የቅድመ አያቶቻቸው የዳዊት ከተማ ቤትልሔም ነበር።

ወደ ቤትልሔም በደረሱ ጊዜ ማረፊያ ስፍራ አልነበራቸውም። ሊያገኙ የቻሉት ብቸኛ ክፍል እንስሶች የሚያድሩበት ስፍራ ነበረ። ሕፃኑ በተወለደ ጊዜ የሚያስተኙበት አልጋ ስላልነበረ እናቱ በከብቶች መመገቢያ ገንዳ አስተኛችው። ስሙንም ኢየሱስ አሉት።

በዚያ ሌሊት በአቅራቢያው ባለ ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን የሚጠብቁ ጥቂት እረኞች ነበሩ። በድንገት የሚያበራ መልአክ ታያቸው፣ እነርሱም ፈሩ። መልአኩ፣ ‹‹አትፍሩ፣ ምክንያቱም ለእናንተ የምነግራችሁ የምሥራች አለኝ። መሲሑ ጌታ በቤተልሔም ተወልዶአል!››።

“ሄዳችሁ ሕፃኑን ፈልጉ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎና በእንስሶች መመገቢያ ገንዳ ተኝቶ ታገኙታላችሁ።” አለ። ድንገትም ሰማያት ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በሰማይ ይሁን! ሰላምም እግዚአብሔር ለሚወደው ሕዝብ በምድር ላይ ይሁን!›› እያሉ እግዚአብሔርን በሚያመሰግኑ መላእክት ተሞሉ።

እረኞች ኢየሱስ ወደ ነበረበት ስፍራ ፈጥነው ደረሱና ልክ መልአኩ እንደ ነገራቸው በእንስሶች መመገቢያ ገንዳ ተኝቶ አገኙት፡፡ በጣም ደስ አላቸው፡፡ እረኞቹ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ በጎቻቸው ወደ ነበሩባቸው ሜዳዎች ተመለሱ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሆኑ ጠቢባን በሰማይ አንድ ያልተለመደ ኮከብ ዐዩ፡፡ ዐዲስ የአይሁድ ንጉሥ የተወለደ መሆኑን እንደሚያመለክትም ተገነዘቡ፡፡ ስለዚህ ይህንን ንጉሥ ለማየት በጣም ረጅም ርቀት ተጓዙ፡፡ ወደ ቤተ ልሔም መጡና ኢየሱስና ወላጆቹ የነበሩበትን ቤት አገኙት፡፡

ጠቢባኑ ኢየሱስን ከእናቱ ጋር ባዩት ጊዜ ወድቀው ሰገዱለት፡፡ ለኢየሱስም ውድ ስጦታዎች ሰጡት፡፡ ከዚያም ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 1፤ ሉቃስ 2፡፡
24. ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀ

የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ ዮሐንስ አድጎ ነቢይ ሆነ፡፡ የሚኖረውም በምድረበዳ ነበር የሚበላውም፣ የበረሐ ማርና አንበጣ ነበር፣የሚለብሰውም ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ነበር፡፡

ብዙ ሕዝብ ዮሐንስን ለመስማት ወደ ምድረ በዳ መጡ፡፡ እርሱም፣ ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ›› እያለ ሰበከላቸው፡፡

ሕዝቡ የዮሐንስን መልእክት በሰሙ ጊዜ፣ ብዙዎች ኃጢአታቸውን ተናዘዙ፣ ዮሐንስም አጠመቃቸው፡፡ ብዙ የሃይማኖት መሪዎችም ደግሞ በዮሐንስ ሊጠመቁ መጡ፣ ነገር ግን ንስሐ አልገቡም ወይም ኃጢአታቸውን አልተናዘዙም፡፡

ዮሐንስ ለሃይማኖት መሪዎቹ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹እናንተ መርዛማ እባቦች! ንስሐ ግቡና ባሕሪያችሁን ለውጡ። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጥና ወደ እሳት ይጣላል።›› ነቢያት ‹‹እነሆ፣ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ።›› በማለት የተናገሩት ትንቢት በሐንስ ተፈጸመ።

አንዳንድ አይሁዶች መሲሕ ስለ መሆኑ ዮሐንስን ጠየቁት፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መለሰ፣ ‹‹እኔ መሲሑ አይደለሁም፣ ነገር ግን ከእኔ በኋላ የሚመጣ አንድ ሰው አለ፡፡እርሱ እጅግ ታላቅ ስለሆነ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ልፈታ እንኳ አይገባኝም፡፡››

በቀጣዩ ቀን፣ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ መጣ፡፡ ዮሐንስ ባየው ጊዜ፣ ‹‹ተመልከቱ! እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› አለ፡፡

ዮሐንስ ኢየሱስን፣ ‹‹እኔ አንተን ለማጥመቅ ተገቢ ሰው አይደለሁም። ይልቁን አንተ እኔን ማጥመቅ አለብህ›› አለው። ኢየሱስ ግን፣ ‹‹ ይህ መደረግ ያለበት ትክክለኛ ነገር ስለሆነ አንተ እኔን ማጥመቅ አለብህ›› አለው። ስለዚህ ኢየሱስ ከቶ ኃጢአት ባይሠራም እንኳ ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው።

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኃው እንደ ወጣ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል ታየና ወርዶ በእርሱ ላይ ዐረፈ፡፡ በዚሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ድምፅ ከሰማይ፣ ‹‹አንተ እኔ የምወድህ ልጄ ነህ፣ በአንተም በጣም ደስ ብሎኛል›› ብሎ ተናገረ፡፡

እግዚአብሔር ለዮሐንስ፣ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ይወርድና አንተ በምታጠምቀው በአንድ ሰውዬ ላይ ያርፋል።ያ ሰያውዬ የእግዚአብሔር ልጅ ነው›› ብሎ ተናግሮት ነበር። አንድ አምላክ ብቻ አለ። ነገር ግን ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔር አብ ሲናገር ሰማ፣ እግዚአብሔር ወልድን ዐየ፣ እርሱም ኢየሱስ ነው፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ዐየ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 3፤ ማርቆስ 1፡9-11፤ ሉቃስ 3፡1-23፡፡
25. ሰይጣን ኢየሱስን ፈተነው

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፣ እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ ከዚያም ሰይጣን ወደ ኢየሱስ መጣና ኃጢአት እንዲሠራ ኢየሱስን ፈተነው፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ፣እነዚህን ድንጋዮች ወደ እንጀራ ለውጥ›› በማለት ሰይጣን ኢየሱስን ፈተነው፡፡

ኢየሱስ፣ ‹‹‹ሰዎች ለመኖር እንጀራ ብቻ አያስፈልጋቸውም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚናገረው እያንዳንዱ ቃል ያስፈልጋቸዋል› ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተጽፎአል!›› ብሎ መለሰለት፡፡

ከዚያም ሰይጣን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ ጫፍ ወሰደውና፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ራስህን ወደ ታች ወርውር፣ ምክንያቱም፣ ‹ድንጋይ እግርህን እንዳይመታህ ይሸከሙህ ዘንድ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዛል ተብሎ ተጽፎል››› አለ፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ቃል በመጥቀስ ለሰይጣን መለሰለት፡፡ ‹‹በእግዚአብሔር ቃል፣ ‹ጌታ አምላክህን አትፈታተነው› ተብሎ ተጽፎአል›› አለው፡፡

ከዚያም ሰይጣን የዓለምን መንግሥታትና ክብራቸውን ሁሉ ዐሳየውና፣ ‹‹ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ›› አለ፡፡

ኢየሱስ፣ ‹‹ከኔ ራቅ፣ አንተ ሰይጣን! በእግዚአብሔር ቃል፣ ‹ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ› ተብሎ ተጽፎአል›› አለው፡፡

ኢየሱስ ለሰይጣን ፈተና አልተሸነፈም፣ ስለዚህ ሰይጣን ለጊዜው ትቶት ሄደ፡፡ ከዚያ በኋላ መላእክት መጥተው ኢየሱስን አገለገሉት፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 4፡1-11፤ ማርቆስ 1፡12-13፤ ሉቃስ 4፡1-13፡፡
26. ኢየሱስ አገልግሎቱን ጀመረ

ኢየሱስ የሰይጣንን ፈተና ካሸፈነ በኋላ፣ ይኖርበት ወደ ነበረው ወደ ገሊላ አውራጃ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልቶ ተመለሰ። ከቦታ ወደ ቦታም እየሄደ አስተማረ። ሁሉም ሰው ስለ እርሱ መልካም ይናገር ነበር።

ኢየሱስ በልጅነቱ ይኖረበት ወደ ነበረው ወደ ናዝሬት ከተማ ተመለሰ። በሰንበት ቀንም አይሁድ እግዚአብሔርን ወደሚያመልኩበት ስፈራ ሄደ። ያነብ ዘንድ የነቢዩን የኢሳይያስን ጥቅልል መጽሐፍ ሰጡት። ኢየሱስ ጥቅልል መጽሐፉን ከፍቶ በከፊል ለሕዝቡ አነበበላቸው።

ኢየሱስ፣ ‹‹ለድሆች የምሥራችን፣ ለተማረኩት ነጻትን፣ ለዕውሮች ማየትን፣ ለታሰሩትም መፈታትን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰጥቶኛል፡፡ ይህች የተወደደችው የጌታ ዓመት ነች›› ብሎ አነበበ፡፡

ከዚያም ኢየሱስ ተቀመጠ፡፡ ሁላቸውም ቀርበው ተመለከቱት፡፡አሁን ያነበበው የእግዚአብሔር ቃል ስለ መሲሑ የሚናገር መሆኑን ያውቁ ነበር፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ይህ ያነበብኩላችሁ ቃል ልክ አሁን እየተፈጸመ ነው ›› አለ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ተደነቁ፡፡ ‹‹ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?›› አሉ፡፡

ከዚያም ኢየሱስ፣ ‹‹ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር የታወቀ ነው፣ በነቢዩ ኤልያስ ዘመን፣ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ለሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ ባልዘነበ ጊዜ መበለት የሆነችውን ሴት እንዲረዳ እግዚአብሔር ኤልያስ ከሌላ አገር ወደ ሆነችው መበለት ላከ እንጂ ከእስራኤል የሆነች መበለትን እንዲረዳ አልላከውም፡፡››

ኢየሱስ መናገሩን በቀጠል፣ ‹‹በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል የቆዳ ሕመም የያዛቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ኤልሳዕ አንዳቸውንም አልፈወሰም፡፡ ነገር ግን የእስራኤል ጠላቶች አዛዥ የነበረውን የንዕማንን ቆዳ በሽታ ብቻ ፈወሰ፡፡›› ኢየሱስን ይሰሙ የነበሩት ሕዝብ አይሁዳውያን ነበሩ፡፡ ስለዚህ ይህን ሲናገር በሰሙት ጊዜ ተናደዱበት፡፡

የናዝሬት ሕዝብ ኢየሱስን ከአምልኮው ቦታ ጐተቱትና ወርውረው ሊገድሉት ወደ ገደል አፋፍ ወሰዱት፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በሕዝቡ መካከል ተራመደና ወደ ናዝሬት ከተማ ሄደ፡፡

ከዚያም ኢየሱስ በገሊላ አውራጃ ሁሉ ተዘዋወረ፣ ብዙ ሕዝብም ወደ እርሱ መጡ፡፡ ማየት፣ መራመድ፣ መስማት፣ ወይም መናገር የማይችሉትን ጨምሮ ብዙ የታመሙ ወይም የአካል ጕዳተኞች የሆኑ ሰዎችን ወደ እርሱ አመጡ ኢየሱስም ፈወሳቸው፡፡

አጋንንት የነበሩባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፡፡ በኢየሱስ ትእዛዝ አጋንንቱ ከሰዎቹ ወጡ፣ ብዙ ጊዜም፣ ‹‹አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!›› ብለው ይጮኹ ነበር፡፡ ሕዝቡ ተደነቁና እግዚአብሔርን አመለኩ፡፡

ከዚያም ኢየሱስ የእርሱ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትን ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጠ፡፡ ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር እየተጓዙ ከእርሱ ተማሩ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 4፡12-25፤ ማርቆስ 1፡14-15፣ 35-39፤ 3፡13-21፤ ሉቃስ 4፡14-30፣ 38-44፡፡
27.የደጉ ሳምራዊ ታሪክ

አንድ ቀን አንድ የአይሁድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ወደ ኢየሱስ መጣ፣ ‹‹መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?›› አለው፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹በእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈው ምንድን ነው?›› ብሎ መለሰለት፡፡

ሕግ ዐዋቂውም ‹‹የእግዚአብሔር ሕግ፣ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም ዐሳብህም ውደድ። ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ›› ይላል ብሎ መለሰ። ኢየሱስ፣ ‹‹ትክክል ነህ! ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ›› አለው።

ነገር ግን ሕግ ዐዋቂው ጻድቅ መሆኑን ለማረጋገጥ ፈለገ፣ ስለዚህ፣ ‹‹ባልንጀራዬ ማን ነው?›› ብሎ ጠየቀ፡፡

ኢየሱስ ምሳሌ በመናገር ለሕግ ዐዋቂው መለሰለት። ‹‹ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ የነበረ አንድ አይሁዳዊ ነበረ።››

‹‹ሰውዬው በመጓዝ ላይ እያለ ወንበዴዎች አጠቁት፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ ወሰዱበትና እጅግ ደበደቡት፡፡ በሞት አፋፍም ጥለውት ሄዱ፡፡››

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ አይሁዳዊ ካህን በዚያም መንገድ ይጓዝ ነበር፡፡ ይህ የሃይማኖት መሪ የተዘረፈውንና የተደበደበውን ሰው ባየ ጊዜ መንገዱን ቀይሮ ሳይረዳው ትቶት ሄደ።››

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ አንድ ሌዋዊ መጣ፡፡ (ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ካህናቱን የሚረዱ የአይሁድ ነገድ ነበሩ፡፡) ሌዋዊውም ደግሞ እንዳይረዳው መንገዱን ቀይሮ የተዘረፈውንና የተደበደበውን ሰው ችላ ብሎ ትቶት ሄደ፡፡››

በዚያ መንገድ የወረደው የሚቀጥለው ሰው ሳምራዊ ነበር፡፡ (ሳምራውያን የሌሎች አገሮች ሰዎችን ያገቡ የአይሁድ ዝርያዎች ነበሩ፡፡ ሳምራውያንና አይሁዳውያን አይዋደዱም ነበር፡፡) ነገር ግን ሳምራዊው አይሁዳዊውን ባየ ጊዜ በጣም አድርጎ ራራለት፡፡ ስለዚህ ተንከባከበውና ቊስሉን አሰረለት፡፡››

‹‹ከዚያ በኋላ ሳምራዊው ሰውዬውን አንሥቶ በራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው ተንከባከበውም፡፡››

‹‹በማግሥቱም ሳምራዊው ጕዞውን መቀጠል ግድ ሆነበት፡፡ ለእንግዶች ማረፊያ ኃላፊ ገንዘብ ሰጠውና፣ ‹‹እባክህ ተንከባከበው፣ ከዚህ ሌላ ገንዘብ የምታወጣ ከሆነ በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ›› አለው፡፡

ኢየሱስም ሕግ ዐዋቂውን፣ ‹‹ምን ታስባለህ? ለተዘረፈውና ለተደበደበው ሰው ባልንጀራው ከሦስቱ ሰዎች የትኛው ነበር?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ ‹‹ምሕረት ያደረገለት ነበር›› ብሎ መለሰለት፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹አንተም ሄደህ እንደዚሁ አድርግ›› ብሎ ነገረው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 10፡25-37፡፡
28. ባለ ጠጋው ወጣት

አንድ ቀን አንድ ባለጠጋ ወጣት ገዥ ወደ ኢየሱስ መጣና፣ ‹‹ቸር መምህር፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ስለ ምን ‹ቸር› ትለኛለህ? ቸር አንድ ብቻ አለ፣ እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን አንተ የዘላለም ሕይወት እንዲኖርህ ከፈለግህ ለእግዚአብሔር ሕግ ታዘዝ›› አለው፡፡

‹‹የትኞቹን ልታዘዝ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‹‹አትግደል፡፡ አታመንዝር፡፡ አትስረቅ፡፡ አትዋሽ፡፡ አባትህንና እናትህን አክብር፣ ባልጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፡፡››

ነገር ግን ወጣቱ፣ ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ እነዚህን ሕጎች ሁሉ ፈጽሜአለሁ፡፡ ለዘላለም ለመኖር ሌላስ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?›› አለ፡፡ ኢየሱስ ዐየውና ወደደው፡፡

ኢየሱስ፣ ‹‹ፍጹም ለመሆን ብትፈልግ፣ ያለህን ንብረት ሁሉ ሽጥና ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም የሀብት መዝገብ ታገኛለህ፡፡ ከዚያም በኋላ ናና ተከተለኝ›› ብሎ መለሰለት፡፡

ወጣቱ፣ ኢየሱስ የተናገረውን በሰማ ጊዜ፣ በጣም ሀብታም ነበርና ያለውን ንብረት ሁሉ ለድኻ መስጠት ስላልፈለገ በጣም ዐዘነ፡፡ ከኢየሱስ ፊቱን አዞረና ሄደ፡፡

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፣ ‹‹ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው! አዎ፣ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፡፡››

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ ደነገጡና፣ ‹‹ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?›› አሉ፡፡

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና፣ ‹‹ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል›› አለ፡፡

ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ ‹‹እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፡፡ ዋጋችን ምን ይሆን?›› አለው፡፡

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‹‹ስለ እኔ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን ወይም ንብረትን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል፡፡ ነገር ግን ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፣ ኋለኞችም የሆኑ ብዙዎች ፊተኞች ይሆናሉ፡፡››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 19፡16-30፤ ማርቆስ 10፡17-31፤ ሉቃስ 18፡18-30፡፡
29. የምሕረት የለሹ ባሪያ ታሪክ

አንድ ቀን ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ ‹‹መምህር ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው?እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ሰባት ጊዜ አይደለም፣ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ›› አለው፡፡ ኢየሱስ ይህን ሲል ሁልጊዜ ይቅር ማለት አለብን ማለቱ ነው፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ተናገረ፡፡

ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ከባርያዎቹ ጋር ሒሳብ ሊተሳሰብ የፈለገን አንድ ንጉሥ ትመስላለች፡፡ ከባሮቹ አንዱ የ200,000 ዓመታት ደመወዝ የሚያክል ከፍተኛ ዕዳ ነበረበት፡፡››

ባሪያው ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ፣ ንጉሡ፣ ‹‹ዕዳውን ይከፍል ዘንድ ይህን ሰውና ቤተ ሰቡን ለባርነት ሽጡአቸው›› አለው፡፡

‹‹ባሪያው በንጉሡ ፊት ተንበረከከና፣ ‹እባክህን ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ› አለው፡፡ ንጉሡ ለባሪያው አዘነለት፣ ዕዳውንም ሁሉ ሰረዘለትና እንዲሄድ ለቀቀው፡፡››

‹‹ነገር ግን ባሪያው ከንጉሡ ዘንድ በወጣ ጊዜ፣ የአራት ወር ደመወዝ የሚያክል ገንዘብ የእርሱ ዕዳ ያለበትን ከባልንጀሮቹ ባሪያዎች አንዱን አገኘ፡፡ ባሪያውም ባልንጀራውን ባሪያ ያዘውና፣ ‹ዕዳህን ክፈለኝ!››› አለው፡፡

‹‹ባልንጀራው ባሪያ በፊቱ ተንበርክኮ፣ ‹እባክህን ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ› አለው፡፡ ነገር ግን ያ ባሪያ ባልንጀራ ባሪያውን ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ በወኅኒ ጣለው፡፡››

‹‹ሌሎች ባሮችም የሆነውን ነገር ዐይተው እጅግ ተረበሹ፡፡ ወደ ንጉሡ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ነገሩት፡፡››

‹‹ንጉሡ ባሪያውን ጠራና፣ ‹አንተ ክፉ ባሪያ! ስለ ለመንኸኝ ዕዳህን ሁሉ ተውሁልህ፡፡ አንተም እንዲሁ ማድረግ ነበረብህ› አለው፡፡ ንጉሡ በጣም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ክፉውን ባሪያ በወኅኒ ጣለው፡፡››

ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹‹ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ የሰማይ አባቴ በእናንተም እንዲሁ ያደርግባችኋል፡፡››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 18፡21-35፡፡
30. ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ

ኢየሱስ በተለያዩ ብዙ መንደሮች እንዲሰብኩና ሰዎችን እንዲያስተምሩ ሐዋርያቱን ላከ፡፡ እነርሱም ኢየሱስ ወደ ነበረበት በተመለሱ ጊዜ፣ ያደረጉትን ነገር ነገሩት፡፡ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከሐይቁ ማዶ ጸጥታ ወዳለበት ቦታ አብረውት እንዲሄዱና ጥቂት እንዲያርፉ ጋበዛቸው፡፡ ስለዚህ ጀልባ ውስጥ ገቡና ወደ ሐይቁ ማዶ ሄዱ፡፡

ነገር ግን በጀልባው ሲሄዱ ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ያዩአቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሊቀድሙአቸው በሐይቁ ዳርቻ ሮጡ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ማዶ በደረሱ ጊዜ፣ በጣም ብዙ ሰዎች አስቀድመው እዚያ ደርሰው ይጠባበቁአቸው ነበር፡፡

ሕዝቡ ሴቶችና ልጆች ሳይቈጠሩ ከ5000 በላይ ወንዶች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ለሕዝቡ እጅግ አዘነላቸው፡፡ ለኢየሱስ እነዚህ ሕዝብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ አስተማራቸውና በመካከላቸው የነበሩትን በሽተኞች ፈወሳቸው፡፡

ቀኑ ሊመሽ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብለው ለኢየሱስ ነገሩት፣ ‹‹ጊዜው መሽቶአል፤ በአቅራቢያውም ከተሞች የሉም፡፡ ስለዚህ የሚበሉትን ነገር ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብታቸው፡፡››

ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው!›› አላቸው፡፡ እነርሱም፣ ‹‹ይህን ማድረግ እንዴት እንችላለን? ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ ብቻ ነው›› ብለው መለሱለት፡፡

ሃምሳ ሃምሳ ሆነው ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ ለሕዝቡ ይነግሩ ዘንድ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፡፡

ከዚያም ኢየሱስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ተመለከተ፣ ስለ ምግቡም እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚያም ኢየሱስ እንጀራውንና ዓሣውን ቈረሰ፡፡ የቈረሰውን ለሕዝቡ እንዲያቀርቡም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ምግቡን ማደላቸውን ቀጠሉ፣ በፍጹም አያልቅም ነበር! ሕዝቡ ሁሉ በልተው ጠገቡ፡፡

ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ቊርስራሹን ምግብ ሰበሰቡ፣ እርሱም ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ነበር! ምግቡ ሁሉ የመጣው ከአምስቱ እንጀራና ከሁለቱ ዓሣ ነበር፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 14፡13-21፤ ማርቆስ 6፡31-44፤ ሉቃስ 9፡10-17፤ ዮሐንስ 6፡5-15፡፡
31. ኢየሱስ በውሃ ላይ ተራመደ

ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡን እያሰናበተ እያለ ጀልባ ውስጥ ገብተው እየቀዘፉ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፡፡ ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፡፡ በዚያ ኢየሱስ ብቻውን ነበር፣ እስከ እኩለ ሌሊትም ጸለየ፡፡

በዚያን ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ጀልባቸውን እየቀዘፉ ነበር፣ ይሁን እንጂ በእኩለ ሌሊት የደረሱት ወደ ሐይቁ አጋማሽ ብቻ ነበር፡፡ ነፋሱ በእነርሱ ላይ በኃይል ይነፍስ ስለ ነበር የሚቀዝፉት በጣም በችግር ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መጸለዩን ጨረሰና ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ፡፡ በውሃው ላይ እየተራመደ ሐይቁን አቋርጦ ወደ ጀልባቸው መጣ!

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ባዩ ጊዜ በጣም ፈሩ፣ ምክንያቱም ምትሐት ያዩ መሰላቸው፣ ኢየሱስም እንደ ፈሩ ዐወቀ፣ ስለዚህ ወደ እነርሱ ተጣራና፣ ‹‹አትፍሩ፡፡ እኔ ነኝ!›› አላቸው፡፡

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ ‹‹መምህር ሆይ፣ አንተስ ከሆንክ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዝ›› አለው፡፡ ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ ‹‹ና!›› አለው፡፡

ስለዚህ ጴጥሮስ ከጀልባው ወጣና በውሃው ላይ ወደ ኢየሱስ መራመድ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ትንሽ እንደ ተራመደ ዓይኖቹን ከኢየሱስ ዞር አደረገና ማዕበሉን ማየትና ብርቱውን ነፋስም መስማት ጀመር፡፡

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ፈራና በውሃው መስጠም ጀመረ፡፡ ‹‹መምህር ሆይ፣ አድነኝ!›› ብሎ ጮኸ፡፡ ኢየሱስ ወዲያው እጆቹን ዘረጋና ያዘው፡፡ ከዚያም ጴጥሮስን፣ ‹‹አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርህ?›› አለው፡፡

ጴጥሮስና ኢየሱስ ወደ ጀልባው በገቡ ጊዜ፣ ነፋሱ ወዲያውኑ ቆመና ውሃው ጸጥ አለ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተደነቁ፡፡ ‹‹በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› እያሉ ለኢየሱስ ሰገዱለት፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 14፡22-23፤ ማርቆስ 6፡45-52፤ ዮሐንስ 6፡16-21፡፡
32. ኢየሱስ ርኵስ መንፈስ የያዘውን ሰውና የታመመችውን ሴት ፈወሰ

አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ሐይቁን አቋርጠው የጌርጌሴኖን ሰዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ ሄዱ፡፡

ወደ ሐይቁ ማዶ በደረሱ ጊዜ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ሮጦ ወደ ኢየሱስ መጣ፡፡

ይህ ሰው ማንም ሊቈጣጠረው የማይችል እጅግ ብርቱ ነበረ፡፡ እንዲያውም ሰዎች እጆቹንና እግሮቹን በሰንሰለት አስረውት ነበር፣ ነገር ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ ነበር፡፡

ሰውዬው በአካባቢው ባሉ መቃብሮች መካከል ይኖር ነበር፡፡ ይህ ሰው ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ ይጮኽ ነበር፡፡ ልብስም አይለብስም ነበር፣ ሰውነቱንም በተደጋጋሚ በድንጋይ ይቧጭር ነበር፡፡

ሰውዬው ወደ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ፣ በፊቱ በጉልበቱ ወድቆ ሰገደለት፡፡ ኢየሱስ ርኵስ መንፈሱን፣ ‹‹ከዚህ ሰው ውጣ!›› አለው፡፡

ርኵስ መንፈሱ ያለበት ሰው ከፍ ባለ ድምፅ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ ከእኔ ምን ትፈልጋለህ? እባክህን አታሠቃየኝ!›› ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ርኵስ መንፈሱን፣ ‹‹ስምህ ማን ነው?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ ‹‹ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው›› ብሎ መለሰ፡፡ (‹ሌጌዎን› በሮማ ጦር ሠራዊት ብዙ ሺህ ወታደሮችን የያዘ ክፍል ነበር፡፡)

ርኵሳን መናፍስቱ፣ ‹‹እባክህን ከዚህ አካባቢ አታርቀን!›› ብለው ኢየሱስን ለመኑት፡፡ በአቅራቢያው ባለ ኮረብታ ላይ የእሪያ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ርኵሳን መናፍስቱ ኢየሱስን፣ ‹‹እባክህን በዚህ ፈንታ ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን!›› ብለው ለመኑት፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ሂዱ!›› አላቸው፡፡

ርኵሳን መናፍስቱ ከሰውዬው ወጡና ወደ እሪያዎቹ ገቡ፡፡ እሪያዎቹ ከአፋፉ ቊልቊል ሮጡና በሐይቁ ሰጠሙ፡፡ በመንጋው 2,000 ያህል እሪያዎች ነበሩ፡፡

እሪያዎቹን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ ወደ ከተማ ሮጡና ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ላገኙት ሰው ሁሉ ተናገሩ፡፡ የከተማው ሰዎች መጡና ርኵሳን መናፍስት የነበሩበትን ሰው ዐዩ፡፡ ልብሱን ለብሶ ጤናማ ሰው ሆኖ በጸጥታ ተቀምጦ ነበር፡፡

ሰዎቹ በጣም ፈርተው ነበርና ኢየሱስን እንዲሄድ ጠየቁት፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ጀልባ ውስጥ ገባና ለመሄድ ተዘጋጀ፡፡ ርኵሳን መናፍስት የነበሩበት ሰውዬም ከኢየሱስ ጋር ለመሄድ ለመነው፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ፣ ‹‹አይደለም፣ ወደ ቤትህ ሄደህ እግዚአብሔር ስላደረገልህ ነገር ሁሉና እንዴት እንደ ማረህ ለወዳጆችህና ለቤተ ሰብህ እንድትነግር እፈልጋለሁ›› አለው፡፡

ስለዚህ ሰውዬው ሄደና ኢየሱስ ስላደረገለት ነገር ለሁሉም ሰው ተናገረ፡፡ ታሪኩን የሰማ ሰው ሁሉ በአድናቆትና በአግራሞት ተሞላ፡፡

ኢየሱስ ወደ ሐይቁ ማዶ ተመለሰ፡፡ እዚያ በደረሰ ጊዜ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰበሰቡና አጨናነቁት፡፡ በሕዝቡ መካከል ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስባት የነበረች ሴት ነበረች፡፡ እንዲፈውሱአት ገንዘብዋን ሁሉ ለሐኪሞች ከፍላ ነበር፣ ነገር ግን ባሰባት እንጂ አልተፈወሰችም፡፡

ኢየሱስ ብዙ በሽተኞችን እንደ ፈወሰ ሰምታ ነበርና፣ ‹‹የኢየሱስን ልብስ ብቻ ብዳስስ ያኔ እኔም እንደምፈወስ እርግጠኛ ነኝ!›› ብላ ዐሰበች፡፡ ስለዚህ ከኢየሱስ ኋላ መጣችና ልብሱን ዳሰሰች፡፡ ልብሱን እንደ ዳሰሰች ወዲያውኑ ደምዋ ቆመ!

ወዲያውኑ፣ ኢየሱስ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፡፡ ስለዚህ ወደ ኋላ ዞረና፣ ‹‹ማን ነው የዳሰሰኝ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹በዙሪያህ የተሰበሰቡና የሚያጋፉህ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ለምን ‹ማን ዳሰሰኝ› ብለህ ትጠይቃለህ?›› ብለው መለሱለት፡፡

ሴቲቱ በጣም ፈርታ እየተንቀጠቀጠች በኢየሱስ ፊት ተደፋች፡፡ ከዚያም ምን እንዳደረገችና እንደ ተፈወሰች ነገረችው፡፡ ኢየሱስም፣ ‹‹እምነትሽ አድኖሻል፡፡በሰላም ሂጂ›› አላት፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 8፡28-34፤ 9፡20-22፤ ማርቆስ 5፡1-20፤ 5፡24-34፤ ሉቃስ 8፡26-39፤ 8፡42-48፡፡
33. የአርሶ አደሩ ታሪክ

አንድ ቀን ኢየሱስ በሐይቁ ዳርቻ አጠገብ በጣም ብዙ ሕዝብ እያስተማረ ነበር፡፡ ኢየሱስ ሊናገራቸው በቂ ቦታ ለማግኘት በውሃው ዳርቻ በጀልባ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ በጣም ብዙ ሰዎች ሊሰሙት መጡ፡፡ በጀልባው ተቀመጠና ሕዝቡን አስተማረ፡፡

ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ተናገረ፡፡ ‹‹አንድ አርሶ አደር ዘር ሊዘራ ወጣ፡፡ በእጁ ዘሩን ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፣ ወፎችም መጥተው ያን ዘር በሙሉ በሉት፡፡››

‹‹ሌላው ዘር ብዙ አፈር በሌለበት በአለታማ መሬት ላይ ወደቀ፣ ዘሩም ቶሎ ወዲያው በቀለ፤ ነገር ግን ብዙ አፈር ስለሌለ ሥሩ ወደ መሬት መጥለቅ አልቻለም፡፡ ፀሐይዋ በወጣችና በሞቀች ጊዜ፣ ቡቃያው ጠወለገና ደረቀ፡፡››

‹‹አሁንም ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፡፡ ይህ ዘር መብቀል ጀመረ፣ ነገር ግን እሾኹ አነቀው፡፡ ስለዚህ በእሾኻማው መሬት ላይ የበቀለው ቡቃያ ምንም ፍሬ አላፈራም፡፡››

‹‹ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ይህ ዘር በቀለና አንዱ 30፣ አንዱ 60፣ አንዱም መቶ ፍሬ ሰጠ፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!››

ይህ ምሳሌ ደቀ መዛሙርቱን ግራ አጋባቸው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አብራራላቸው፣ ‹‹ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በመንገዱ ዳር የተዘራው ዘር የሚያሳየው የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን አያስተውለውም፣ ዲያብሎስም ቃሉን ይወስድበታል፡፡››

‹‹በአለታማ መሬት የተዘራው ዘር የሚያሳየው የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በደስታ የሚቀበለው ሰው ነው፡፡ ነገር ግን መከራ ወይም ስደት በሚያጋጥመው ጊዜ እምነቱን ይተዋል፡፡››

‹‹በእሾኻማው መሬት ላይ የተዘራው ዘር የሚያሳየው የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የዚህ ዓለም ዐሳብ፣ ባለጠግነትና ደስታ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያንቃል፡፡ ከዚህ የተነሣ፣ የሰማው ትምህርት ፍሬ አያፈራም፡፡

‹‹በመልካሙ መሬት ላይ የተዘራው ዘር የሚያሳየው ግን የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፣ የሚያምነውና ፍሬ የሚያፈራ ሰው ነው፡፡››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 13፡1-8፣ 18-23፤ ማርቆስ 4፡1-8፣ 13-20፤ ሉቃስ 8፡4-15፡፡
34.ኢየሱስ ሌሎች ታሪኮችን አስተማረ

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን አስተማረ፡፡ ለምሳሌ፣ እንዲህ አለ፣ ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ሰው በማሳው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፡፡ እርስዋም ከሁሉ ዘር የምታንስ ነች፡፡››

‹‹ነገር ግን የሰናፍጭ ዘር ባደገች ጊዜ አዕዋፍ መጥተው እስኪሰፍሩ ድረስ በአትክልት ቦታ ካሉ ተክሎች ሁሉ ትበልጣለች፡፡

ኢየሱስ ሌላ ምሳሌ ተናገረ፣ ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ከዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፡፡

‹‹ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ሰው በእርሻ ውስጥ የሸሸገውን የሀብት መዝገብ ትመስላለች፡፡ ሌላ ሰው መዝገቡን አገኘውና እንደ ገና ቀበረው፡፡ በጣም በደስታ ተሞልቶ ነበርና ሄዶ ያለውን ነገር ሁሉ ሸጠና በገንዘቡ እርሻውን ገዛው፡፡››

‹‹ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ ትመስላለች፡፡ የዕንቊ ነጋዴ ባገኛት ጊዜ ያለውን ነገር ሁሉ ሸጠና ገዛት፡፡››

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ በራሳቸው መልካም ሥራ ለሚታመኑና ሌሎችን ለሚንቁ አንዳንድ ሰዎች ምሳሌ ተናገረ፡፡ ‹‹ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡ አንዱ ቀረጥ ሰብሳቢ ሲሆን፣ ሌላው የሃይማኖት መሪ ነበር››፡፡

‹‹የሃይማኖት መሪው እንዲህ ብሎ ጸለየ፣ ‹እግዚአብሔር ሆይ፣ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ እንደዚሁም እንደዚህኛው ቀረጥ ሰብሳቢ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ፡፡››

‹‹እኔ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ገንዘብና ንብረት ሁሉ ከዐሥር አንድ አወጣለሁ፡፡››

‹‹ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ከሃይማኖት መሪው ራቅ ብሎ ቆመ፣ ወደ ሰማይ እንኳ አልተመለከተም፡፡ በዚህ ፈንታ፣ ደረቱን በእጁ እየመታ፣ ‹እግዚአብሔር ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ስለ ሆንኩ እባክህን ማረኝ››› አለ፡፡

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፣ እግዚአብሔር የቀረጥ ሰብሳቢውን ጸሎት ሰማና ጻድቅ ነህ አለው፡፡ የሃይማኖት መሪውን ጸሎት ግን አልወደደም፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገውን ሁሉ ያዋርዳል፣ ራሱን የሚያዋርደውን ግን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 13፡31-33፣ 44-46፤ ማርቆስ 4፡30-32፤ ሉቃስ 13፡18-21፤ 18፡9-14፡፡
35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ

አንድ ቀን ኢየሱስ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችንና ሊሰሙት የተሰበሰቡ ሌሎች ኃጢአተኞችን ያስተምር ነበር፡፡

በዚያ የነበሩ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ወዳጆች አድርጎ ሲቀበላቸው ዐዩ፣ እርስ በርሳቸውም ይነቅፉት ጀመር፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፡፡

ሁለት ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‹አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ድርሻ አሁን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ!› አለው፡፡ ስለዚህ አባትዬው ገንዘቡን ለሁለቱ ልጆቹ አካፈላቸው፡፡››

‹‹ታናሹ ልጅ ወዲያውኑ ያለውን ሁሉ ሰበሰበና ሩቅ አገር ሄዶ በኃጢአት የተሞላ ኑሮ እየኖረ ገንዘቡን አጠፋ፡፡

‹‹ከዚያ በኋላ ታናሹ ልጅ በነበረበት አገር ጽኑ ረሀብ ሆነ፣ ምግብ የሚገዛበት ገንዘብም አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የተገኘው ሥራ እሪያዎችን የመመገብ ሥራ ብቻ ስለ ነበር በዚያ ሥራ ገባ፡፡ በጣም ተጐሳቊሎና ተርቦ ስለ ነበር የእሪያዎችን ምግብ እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፡፡››

‹‹በመጨረሻ፣ ታናሹ ልጅ ለራሱ እንዲህ አለ፣ ‹እዚህ ምን እያደረግሁ ነው ያለሁት? የአባቴ አገልጋዮች ሁሉ እንኳ የሚበሉት ብዙ ምግብ አላቸው፣ እኔ ግን እዚህ በረሃብ እሞታለሁ፡፡ ወደ አባቴ ተመልሼ እሄድና ከአገልጋዮቹ እንደ አንዱ እንዲያደርገኝ እለምነዋለሁ፡፡›››

ስለዚህ ታናሹ ልጅ ወደ አባቱ ቤት ተመልሶ መሄድ ጀመረ፡፡ ገና በሩቅ እያለ አባቱ ዐየውና አዘነለት፡፡ ወደ ልጁ ሮጠና አቀፈው ሳመውም፡፡››

ልጁም፣ ‹አባቴ ሆይ፣ እግዚአብሔርንና አንተን በድዬአለሁ፡፡ ከእንግዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም› አለ፡፡

‹‹ነገር ግን አባቱ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ እንዲህ ብሎ ነገረው፣ ‹ፈጥነህ ሂድና ምርጥ ልብስ አምጥተህ ለልጄ አልብሰው! ለጣቱም ቀለበት፤ ለእግሩም ጫማ አድርግለት፡፡ ከዚያም በልተን ፈንጠዝያ እናደርግ ዘንድ የሰባ ፍሪዳ አምጥተህ እረድ፣ ምክንያቱም ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፣ አሁን ሕያው ሆኖአል! ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል!›››

‹‹ስለዚህ ሰዎቹ ፈንጠዝያ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ፣ ታላቅ ወንድሙ ይሠራበት ከነበረው እርሻ ወደ ቤት መጣ፡፡ የሙዚቃና የዘፈን ድምፅም ሰማ፣ ምን እየሆነ ነው ብሎም ተገረመ፡፡››

‹‹ታላቁ ልጅም ታናሽ ወንድሙ ስለ መጣ ሰዎች እየተደሰቱ መሆናቸውን ባወቀ ጊዜ፣ በጣም ስለ ተቈጣ ወደ ቤት ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ አባቱ ወጣና ገብቶ ከእነርሱ ጋር እንዲደሰት ለመነው፣ እርሱ ግን እምቢ አለ፡፡››

ታላቁ ልጅ አባቱን እንዲህ አለው፣ ‹እነዚህን ዓመታት ሁሉ በታማኝነት ለአንተ ሠርቼአለሁ! አንድም ቀን ስታዘኝ እምቢ ብዬህ አላውቅም። ይሁን እንጂ ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንድ ጥቦት ፍየል እንኳ እስከ አሁን ሰጥተኸኝ አታውቅም። ነገር ግን አሁን ይህ ኃጢአት በመሥራት ገንዘብህን ያባከነው ልጅህ ወደ ቤትህ በመጣ ጊዜ፣ የሰባ ፍሪዳ አረድህለት!›

‹‹አባቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‹ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ያለኝም ነገር ሁሉ የአንተ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፣ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል፡፡ ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል! ስለዚህ እኛ መደሰታችን ትክክል ነው›› አለው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 15፡11-32፡፡
36. የኢየሱስ መልክ ተለወጠ

አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን፦ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ብቻቸውን ሊጸልዩ ወደ ረጅም ተራራ ወጡ፡፡(ዮሐንስ የተባለው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ያጠመቀው ዮሐንስ አይደለም፡፡)

ኢየሱስ በመጸለይ ላይ እያለ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፣ ንጻቱም በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ሊያነጻው እስከማይችል ድረስ በጣም ነጭ ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ ሙሴና ነቢዩ ኤልያስ ታዩ፡፡ እነዚህ ሰዎች በመቶዎች ከሚቈጠሩ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ እነርሱም በቅርቡ በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ስለ ኢየሱስ ሞት ከእርሱ ጋር ተነጋገሩ፡፡

ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር በመነጋገር ላይ እያሉ ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ ‹‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ሦስት ዳሶችን አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ እንዲሁም አንድ ለኤልያስ እንሥራ›› አለው፡፡ ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር፡፡

ጴጥሮስ እየተናገረ እያለ፣ ብሩህ ደመና መጥቶ ከበባቸውና ከደመናውም ድምፅ፣ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት›› አለ፡፡ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ፈሩና መሬት ላይ ወደቁ፡፡

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ዳሰሳቸውና፣ ‹‹አትፍሩ፣ ተነሡ›› አላቸው፡፡ ዙሪያቸውን ሲያዩ ከእነርሱ ጋር ያለው ኢየሱስ ብቻ ነበር፡፡

ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ከተራራው ወረዱ፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹በዚህ ስለ ሆነው ነገር አሁን ለማንም አትናገሩ፡፡ እኔ በቅርብ ጊዜ እሞታለሁ፣ ተመልሼም ሕያውም እሆናለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ለሰዎች መናገር ትችላላችሁ፡፡››
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 17፡1-9፤ ማርቆስ 9፡2-8፤ ሉቃስ 9፡28-36፡፡
37. ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሣ

አንድ ቀን ኢየሱስ አልዓዛር በጣም ታሞአል የሚል መልእክት ደረሰው፡፡ አልዓዛርና ሁለቱ እኅቶቹ ማርያምና ማርታ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ይህንን ወሬ በሰማ ጊዜ፣ ‹‹ይህ ሕመም ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም›› አለ፡፡ ኢየሱስ እነርሱን ይወዳቸው ነበር፣ ነገር ግን ለሁለት ቀናት በነበረበት ስፍራ ቆየ፡፡

ሁለቱ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹ወደ ይሁዳ ምድር ተመልሰን እንሂድ›› አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም መልሰው ‹‹ነገር ግን መምህር ሆይ፣ ‹‹ከጥቂት ጊዜ በፊት በዚያ ያሉት ሕዝብ ሊገድሉህ ይፈልጉ ነበር!›› አሉ፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፣ ከእንቅልፉ ማስነሣት አለብኝ›› አላቸው፡፡

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አልዓዛር ተኝቶስ ከሆነ፣ ተሽሎታል›› ብለው መለሱለት፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፣ ‹‹አልዓዛር ሞቶአል፡፡ እናንተ በእኔ ታምኑ ዘንድ እዚያ ባለመኖሬ ደስ ብሎኛል›› ብሎ በግልጽ ነገራቸው።

ኢየሱስ አልዓዛር ወደ ተወለደበት ከተማ በደረሰ ጊዜ፣ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር፡፡ ማርታ ኢየሱስን ልትገናኘው ወጣችና እንዲህ አለች፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ፡፡››

ኢየሱስም መልሶ፣ ‹‹እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ፡፡ በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡ በእኔ የሚያምን ሁሉ ከቶ አይሞትም፡፡ ይህን ታምኛለሽን?›› አላት፡፡ ማርታም፣ ‹‹አዎን፣ ጌታ ሆይ! አንተ መሲሑ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ›› ብላ መለሰችለት፡፡

ከዚያም ማርያም መጣች፡፡ በኢየሱስ እግር ወደቀችና፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር›› አለች፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ነው ያኖራችሁት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹በመቃብር ነው፡፡ ናና እይ›› ብለው ነገሩት፡፡ ከዚያም ኢየሱስ አለቀሰ፡፡

መቃብሩ ዋሻ ነበር፣ ድንጋይም በአፉ ላይ ተገጥሞበት ነበር፡፡ ኢየሱስ ወደ መቃብሩ በደረሰ ጊዜ ‹‹ድንጋዩን አንከባሉት›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ነገር ግን ማርታ፣ ‹‹ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል፡፡ አሁን ይሸታል›› አለችው፡፡

ኢየሱስ፣ ‹‹በእኔ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታይዋለሽ ብዬ አልነገርኩሽምን?›› አላት፡፡ ስለዚህ ድንጋዩን አንከባለሉት፡፡

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመለከተና፣ ‹‹አባት ሆይ፣ ስለምትሰማኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አንተ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፣ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ እዚህ ስለ ቆሙት ስለ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ይህን እላለሁ›› አለ፡፡ ከዚያም ኢየሱስ፣ ‹‹አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና!›› ብሎ ጮኸ፡፡

ስለዚህ አልዓዛር ወጣ! በከፈን እንደ ተገነዘ ነበር፡፡ ኢየሱስም፣ ‹‹ፍቱትና ይሂድ ተዉት!›› አላቸው፡፡ ከአይሁድ ብዙዎች በዚህ ተአምር ምክንያት በኢየሱስ አመኑ፡፡

ነገር ግን የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ቀኑ፣ ስለዚህ ኢየሱስንና አልዓዛርን እንዴት መግደል እንዳለባቸው ለማቀድ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዮሐንስ 11፡1-46፡፡
38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ

አይሁድ በያመቱ የፋሲካን በዓል ያከብሩ ነበር፡፡ ይህም በዓል ከብዙ ምእት ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ቅድመ አያቶቻቸውን ከግብፅ ባርነት እንዴት እንዳዳናቸው ለማስታወስ የሚከበር ነበር፡፡ ኢየሱስ በይፋ መስበኩንና ማስተማሩን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ፣ ይህን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋር ሊያከብር እንደ ፈለገ፣ በዚያም እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፡፡

ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ይሁዳ የሐዋርያቱ ገንዘብ ያዥ ነበር፣ ነገር ግን ገንዘብ ይወድ ነበርና ብዙ ጊዜ ከከረጢቱ ውስጥ ገንዘብ ይሰርቅ ነበር፡፡ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ፣ ይሁዳ ወደ አይሁድ መሪዎች ሄደና ገንዘብ ከሰጡት ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ነገራቸው፡፡ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የአይሁድ መሪዎች እንደ ካዱና ሊገድሉት ያሤሩ እንደ ነበር ያውቅ ነበር፡፡

የአይሁድ መሪዎችም በሊቀ ካህናቱ ተመርተው፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለይሁዳ ሠላሳ ጥሬ ብር ከፈሉት፡፡ ልክ ነቢያት እንደ ተነበዩት ይህ ሆነ፡፡ ይሁዳም ተስማማ፣ ገንዘቡንም ተቀብሎ ሄደ፡፡ ኢየሱስን እንዲይዙት ሊረዳቸው አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ፡፡

በኢየሩሳሌም፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ፋሲካን አከበረ፡፡ በፋሲካው ምግብ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ቈረሰ፡፡ እንዲህም አለ፣ ‹‹እንካችሁ ይህንን ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ነው፡፡ ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡፡›› በዚህ ዓይነት ኢየሱስ ሥጋው ስለ እነርሱ እንደሚሠዋ ነገራቸው፡፡

ከዚያም ኢየሱስ ጽዋን አንሣና፣ ‹‹ይህንን ጠጡ፡፡ ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የዐዲስ ኪዳን ደሜ ነው፡፡ ይህንን በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡፡››

ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል›› አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደንግጠው፣ እንዲህ ያለ ነገር ማን ያደርጋል ብለውም ጠየቁት፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ይህንን ቊራሽ እንጀራ የምሰጠው ሰው እኔን አሳልፎ የሚሰጠኝ እርሱ ነው›› አለ፡፡ ከዚያ በኋላ እንጀራውን ለይሁዳ ሰጠው፡፡

ይሁዳ እንጀራውን ከተቀበለ በኋላ፣ ሰይጣን ገባበት፡፡ ይሁዳ ኢየሱስን እንዲይዙት የአይሁድ መሪዎችን ሊረዳቸው ሄደ፡፡ ጊዜው ማታ ነበር፡፡

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እራት ከበሉ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ሄዱ፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ዛሬ ማታ ሁላችሁም እኔን ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፡፡ ‹እረኛውን እመታለሁ፤ በጎቹም ሁሉ ይበተናሉ› ተብሎ ተጽፎአል›› አለ፡፡

ጴጥሮስ፣ ‹‹ሌሎቹ ሁሉ ቢተዉህ እንኳ፣ እኔ ግን አላደርገውም!›› ብሎ መለሰ፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፣ ‹‹ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ፥ ይፈልጋል፣ ነገር ግን ጴጥሮስ እምነትህ እንዳይደክም ጸልዬልሃለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ዛሬ ማታ ዶሮ ከመጮኹ በፊት እንደውም አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡››

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ለኢየሱስ፣ ‹‹የምሞት እንኳ ቢሆን፣ ከቶ አልክድህም›› አለው፡፡ ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት ሁሉ ይህንኑ አሉ፡፡

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ቦታ ሄደ፡፡ ኢየሱስ ወደ ፈተና እንዳይገቡ እንዲጸልዩ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ብቻውን ሊጸልይ ሄደ፡፡

ኢየሱስ፣ ‹‹አባቴ ሆይ፣ ቢቻልስ ይህን የመከራ ጽዋ እንዳልጠጣው አድርግ፡፡ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን›› ብሎ ሦስት ጊዜ ጸለየ። ኢየሱስ በጣም ታወከ፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲያበረታታው መልአክ ላከ፡፡

ከእያንዳንዱ የጸሎት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ ይመጣ ነበር። እነርሱ ግን ተኝተው ነበር፡፡ ሦስተኛ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ግን፣ ‹‹ተነሡ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ደርሷል›› አለ፡፡

ይሁዳ ከአይሁድ መሪዎች፣ ከወታደሮችና ከብዙ ሕዝብ ጋር መጣ፡፡ ሰይፍና ዱላ ይዘው ነበር፡፡ ይሁዳ ወደ ኢየሱስ መጣና፣ ‹‹መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፡፡ ይህም የአይሁድ መሪዎች ማንን እንደሚይዙ ምልክት ነበር፡፡ ከዚያም ኢየሱስ፣ ‹‹ይሁዳ፣ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠኛለህን?›› አለ፡፡

ወታደሮቹ ኢየሱስን ሲይዙት፣ ጴጥሮስ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ! ይከላከሉልኝ ዘንድ የመላእክት ሠራዊት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ እችል ነበር፤ ነገር ግን አባቴን መታዘዝ አለብኝ›› አለው፡፡ ከዚያም ኢየሱስ የሰውዬውን ጆሮ ፈወሰው፡፡ ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ሸሹ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 26፡14-56፤ ማርቆስ 14፡10-50፤ ሉቃስ 22፡1-53፤ ዮሐንስ 12፡6፤ 18፡1-11፡፡
39. ኢየሱስ ለፍርድ ቀረበ

አሁን ጊዜው እኩለ ሌሊት ነው። ሊቀ ካህናቱ የምርመራ ጥያቄ ይጠይቀው ዘንድ ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ወሰዱት። ጴጥሮስ ራቅ ብሎ ከኋላ ተከተላቸው። ኢየሱስን ወደ ቤቱ ባስገቡት ጊዜ፣ ጴጥሮስ በውጪ ሆኖ እሳት ይሞቅ ነበር።

በቤቱ ውስጥ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለምርመራ አቀረቡት። በእርሱ ላይ የዋሹ ብዙ የሐሰት ምስክሮችን አመጡ። ይሁን እንጂ፣ ቃላቸው እርስ በርሱ አልተስማማም፣ ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ በማንኛውም ነገር ወንጀለኛ መሆኑን ማረጋገጥ አልቻሉም።

በመጨረሻ፣ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ትኵር ብሎ ተመለከተውና፣ ‹‹ንገረን፣ አንተ መሲሑ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህን?›› አለው።

ኢየሱስም፣ ‹‹አዎን ነኝ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተቀምጬ ሳለሁና ከሰማይም ስመጣ ታያለህ›› አለው። ሊቀ ካህናቱ በቊጣ ልብሱን ቀደደና ለሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች፣ ‹‹ምንም ዓይነት ምስክሮች አያስፈልጉንም! የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል ራሳችሁ ሰምታችሁታል። ፍርዳችሁ ምንድን ነው?›› ብሎ ጮኸ።

ሁሉም የአይሁድ መሪዎች፣ ‹‹ሞት ይገባዋል!›› ብለው ለሊቀ ካህናቱ መለሱለት። ከዚያም ኢየሱስን ፊቱን ሸፈኑት፣ ተፉበት፣ መቱት፣ ዘበቱበትም።

ጴጥሮስ ከቤቱ ውጪ በመጠበቅ ላይ እያለ የቤት ሠራተኛ የሆነች ልጅ ዐየችውና፣ ‹‹አንተም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ነበርክ!›› አለችው፡፡ ጴጥሮስ እርስዋ የተናገረችውን ካደ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላዋ የቤት ሠራተኛ ያንኑ ተናገረች፣ ጴጥሮስም እንደገና ካደ፡፡ በመጨረሻ ሕዝቡ ‹‹ሁለታችሁም ከገሊላ ስለሆናችሁ አንተ ከኢየሱስ ጋር መሆንህን እናውቃለን›› አሉ፡፡

ከዚያም ጴጥሮስ፣ ‹‹ይህንን ሰው እኔ አላውቀውም!›› ብሎ ማለ። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ፣ ኢየሱስም ዘወር አለና ጴጥሮስን ተመለከተው።

ጴጥሮስ ከዚያ ሄደና በምሬት አለቀሰ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ፣ የአይሁድ መሪዎች እንዲሞት በኢየሱስ ላይ እንደ ፈረዱበት ዐየ። ይሁዳ በሐዘን ተሞልቶ ሄደና ራሱን ገደለ።

በነጋታው ማለዳ ላይ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ወደ ሮማው ገዥ ወደ ጲላጦስ አመጡት። ጲላጦስ ኢየሱስን ወንጀለኛ ነህ ብሎ ይፈርድበትና በሞት እንዲቀጣ ያደርጋል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ጲላጦስ ኢየሱስን፣ ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ነህን?›› ብሎ ጠየቀው።

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‹‹አንተም ብለሃል፣ ነገር ግን መንግሥቴ ምድራዊ መንግሥት አይደለችም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ፣ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። እኔ ስለ እግዚአብሔር እውነትን ለመናገር ወደ ምድር መጥቼአለሁ። እውነትን የሚወድ ሁሉ እኔን ይሰማኛል።›› ጲላጦስ፣ ‹‹እውነት ምንድን ነው?›› አለ።

ጲላጦስ ከኢየሱስ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሕዝቡ ወጣና፣ ‹‹በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም›› አለ። የአይሁድ መሪዎችና ሕዝቡ ግን፣ ‹‹ስቀለው!›› ብለው ጮኹ። ጲላጦስ፣ ‹‹ወንጀለኛ አይደለም›› ብሎ መለሰላቸው። እነርሱ ግን የበለጠ ጮኹ። ከዚያም ጲላጦስ ለሦስተኛ ጊዜ፣ ‹‹ወንጀለኛ አይደለም!›› አለ።

ጲላጦስ ሕዝቡ ረበሻ ያስነሣል ብሎ ፈራ፣ ስለዚህ ኢየሱስን እንዲሰቅሉት ወታደሮቹን አዘዘ። የሮማ ወታደሮችም ኢየሱስን ገረፉትና ቀይ የነገሥታት ልብስ አለበሱት፣ እንዲሁም የሾኽ አክሊል በራሱ ላይ አደረጉ። ከዚያም፣ ‹‹እነሆ፣ የአይሁድ ንጉሥ!›› እያሉ ዘበቱበት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 26፡57-27፡26፤ ማርቆስ 14፡53-15፡15፤ ሉቃስ 22፡54-23፡25፤ ዮሐንስ 18፡12-19፡16።
40. ኢየሱስ ተሰቀለ

ወታደሮቹ በኢየሱስ ላይ ከዘበቱበት በኋላ፣ ሊሰቅሉት ወሰዱት። የሚሞትበትን መስቀል እንዲሸከም አደረጉት።

ወታደሮቹ ኢየሱስን ‹‹የራስ ቅል›› ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ አመጡትና እጆቹንና እግሮቹን በመስቀል ላይ ጠረቁአቸው። ኢየሱስ ግን፣ ‹‹አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ዐያውቁምና ይቅር በላቸው›› አለ። ጲላጦስ፣ ‹‹የአይሁድ ንጉሥ›› ብለው ምልክት እንዲጽፉና ከኢየሱስ ራስ በላይ በመስቀሉ ላይ እንዲያኖሩት አዘዘ።

ወታደሮቹ በኢየሱስ ልብስ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። ይህንን ባደረጉበት ጊዜ፣ ‹‹ልብሶቼን ተከፋፈሉ፣ በእጀ ጠባቡም ላይ ዕጣ ተጣጣሉበት›› የሚለውን ትንቢት ፈጸሙ።

ኢየሱስ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ። አንደኛው በኢየሱስ ላይ ዘበተበት፣ ሌላኛው ግን፣ ‹‹አንተ እግዚአብሔርን አትፈራም? እኛ ወንጀለኞች ነን፣ ይህ ሰው ግን ወንጀል የለበትም›› አለ። ከዚያም ኢየሱስን፣ ‹‹እባክህን በመንግሥትህ ዐስበኝ›› አለው። ኢየሱስ፣ ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ›› ብሎ መለሰለት።

የአይሁድ መሪዎችና በሕዝቡ መካከል የነበሩ ሌሎች ሰዎች በኢየሱስ ላይ ዘበቱበት። ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ከመስቀል ላይ ውረድና ራስህን አድን! ከዚያ በኋላ እናምንብሃለን›› አሉት።

በዚያ ሰዓት ጊዜው ገና እኩለ ቀን ቢሆንም፣ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ ጨለማውም ከእኩለ ቀን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ፣ ‹‹ተፈጸመ! አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ እሰጣለሁ›› ብሎ ጮኸ፡፡ ከዚያም ራሱን አዘነበለና ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ በሞተ ጊዜ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፣ በቤተ መቅደስ የነበረው ትልቁ መጋረጃም ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡

ኢየሱስ በሞቱ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ለሰዎች ሁሉ መንገድ ከፈተላቸው፡፡ ኢየሱስን ይጠብቅ የነበረው ወታደር የሆነውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ ‹‹በእርግጥ ይህ ሰው ወንጀል የለበትም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ነው›› አለ፡፡

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያመኑ ሁለት የአይሁድ መሪዎች፣ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የኢየሱስን ሥጋ እንዲሰጣቸው ጲላጦስን ለመኑት። ሥጋውን በጨርቅ ገነዙትና ከአለት በተወቀረ መቃብር አኖሩት። ከዚያም የመቃብሩን በር ትልቅ ድንጋይ አንከባልለው ዘጉት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 27፡27-61፤ ማርቆስ 15፡16-47፤ ሉቃስ 23፡26-56፤ ዮሐንስ 19፡17-42።
41. እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን አስነሣው

ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፣ የማያምኑ የአይሁድ መሪዎች ጲላጦስን፣ ‹‹ያ ውሸታም ኢየሱስ፣ ከሦስት ቀን በኋላ ከሙታን እነሣለሁ ብሎአል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን እንዳይሰርቁትና ከሙታን ተነሥቶአል እንዳይሉ መቃብሩ መጠበቅ አለበት›› አሉት፡፡

ጲላጦስ፣ ‹‹ወታደሮችን ውሰዱና መቃብሩን በደንብ እንዲጠብቁ አድርጉ›› አለ። ስለዚህ በመቃብሩ መግቢያ ባለው ድንጋይ ላይ ማኅተም አደረጉና ሥጋውን ማንም እንዳይሰርቀው በዚያ ወታደሮችን አቆሙ።

ኢየሱስ የተሰቀለበት ቀን ማግስት ሰንበት ነበረ። አይሁድ በዚያ ቀን ወደ መቃብር እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ነበር። ስለዚህ ከሰንበት ቀን በኋላ በማለዳ ጥቂት ሴቶች ሥጋው ላይ ሽቱ ለማድረግ ወደ ኢየሱስ መቃብር ሊሄዱ ተዘጋጁ።

በድንገትም ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ። እንደ መብረቅ የሚያበራ መልአክ ከሰማይ ታየ። የመቃብሩን መግቢያ ከድኖ የነበረውን ድንጋይ አንከባለለና ተቀመጠበት። መቃብሩን ይጠብቁ የነበሩት ወታደሮች በፍርሃት እንደ ሞቱ ሰዎች ሆነው መሬት ላይ ወደቁ።

ሴቶቹ ወደ መቃብሩ በደረሱ ጊዜ መልአኩ፣ ‹‹አትፍሩ! ኢየሱስ እዚህ የለም። ልክ እነሣለሁ ብሎ እንደ ተናገረው ከሞት ተነሥቶአል! መቃብሩን ተመልከቱ›› ብሎ ነገራቸው። ሴቶቹ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከቱና የኢየሱስን ሥጋ ያኖሩበትን ስፍራ ዐዩ። ሥጋው በዚያ አልነበረም።

ከዚያም መልአኩ ለሴቶቹ፣ ‹‹ሂዱና ‹ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው››› ብሎ ነገራቸው።

ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተሞልተው ነበር። የምሥራቹን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።

ሴቶቹ የምሥራቹን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በመሄድ ላይ እያሉ፣ ኢየሱስ ታያቸው፣ እነርሱም ሰገዱለት። ኢየሱስ፣ ‹‹አትፍሩ። ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለደቀ መዛሙርቴ ንገሩአቸው። በዚያ ያዩኛል›› አላቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 27፡62-28፡15፤ ማርቆስ 16፡1-11፤ ሉቃስ 24፡1-12፤ ዮሐንስ 20፡1-18።
42. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለሰ

ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ በአቅራቢያው ወዳለች ከተማ እየሄዱ ነበር። ሲጓዙም፣ በኢየሱስ ላይ ስለ ደረሰበት ነገር ሲነጋገሩ ነበር። እርሱ መሲሕ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገው ነበር፣ ነገር ግን እርሱ ተገደለ። አሁን ሴቶቹ እንደ ገና ሕያው ሆኖአል አሉ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የቱን ማመን እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸው ነበር።

ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበና አብሮአቸው መጓዝ ጀመረ፣ እነርሱ ግን ዐላወቁትም ነበር። ስለ ምን ይነጋገሩ እንደ ነበረ ጠየቃቸው፣ እነርሱም ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ኢየሱስን በተመለከተ ስለ ሆኑት አስገራሚ ነገሮች ሁሉ ነገሩት። የሚነጋገሩት በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ከማያውቅ ከእንግዳ ሰው ጋር መስሏቸው ነበር።

ከዚያም ኢየሱስ፣ ስለ መሲሑ የእግዚአብሔር ቃል የተናገረውን አብራራላቸው። መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል፣ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ነቢያት የተናገሩትን አስታወሳቸው። ሁለቱ ሰዎች ሊያድሩባት ወዳሰቡአት ከተማ ሲደርሱ፣ ጊዜው መሽቶ ነበር።

ሁለቱ ሰዎች ከእነርሱ ጋር እንዲያድር ኢየሱስን ጋበዙት፣ እርሱም እሺ አላቸው። እራት ለመብላት በተዘጋጁ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ እግዚአብሔርን አመሰገነ፣ ከዚያም ቈረሰው። ወዲያውኑ ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እርሱ ከዓይናቸው ተሰወረ።

ሁለቱም ሰዎች፣ ‹‹ኢየሱስ ነው! የእግዚአብሔርን ቃል ሲያብራራልን ልባችን ሲቃጠልብን የነበረው ስለዚህ ነው!›› ተባባሉ፡፡ ወዲያውኑ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ በደረሱም ጊዜም ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹ኢየሱስ ሕያው ነው! ዐይተነዋል!›› ብለው ነገሩአቸው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ እየተነጋገሩ እያሉ፣ ኢየሱስ በድንገት በነበሩበት ክፍል በመካከላቸው ተገኘና፣ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን!›› አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ መሰላቸው፣ ኢየሱስ ግን፣ ‹‹ለምን ትፈራላችሁ፤ ትጠራጠራላችሁም? እጆቼንና እግሮቼን እዩ። መናፍስት እንደ እኔ አካል የላቸውም›› አላቸው። መንፈስ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚበላ ነገር እንዲሰጡት ጠየቃቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ሰጡት፣ እርሱም በላ።

ኢየሱስም፣ ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ ነግሬአችኋለሁ›› አለ። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲረዱ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። ‹‹መሲሑ መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ ከረጅም ዘመን በፊት ተጽፎአል›› አላቸው።

“ደግሞም የኃጢአታቸውን ይቅርታ ለማግኘት ሰዎች ሁሉ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ደቀ መዛሙርቴ እንደሚያውጁ በመጻሕፍት ተጽፎአል። እነርሱ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ይህን ያደርጋሉ፣ ከዚያም በሁሉም ስፍራ ወዳሉ የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ይሄዳሉ። እናንተ የእነዚህ ነገሮች ምስክሮች ናችሁ።” አላቸው።

በቀጣዮቹ አርባ ቀናት ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። አንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች በአንድ ጊዜ ታይቷቸው ነበር! እርሱ ሕያው መሆኑን በብዙ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋገጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱ፣ የሕዝብ ወገኖችን ሁሉ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው። እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።››

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ ከአርባ ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ ወርዶ ኃይልን እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ›› አላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ወጣ፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረችው፡፡ ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ሊገዛ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 28፡16-20፤ ማርቆስ 16፡12-20፤ ሉቃስ 24፡13-53፤ ዮሐንስ 20፡19-23፤ የሐዋርያት ሥራ 1፡1-11።
43. ቤተ ክርስቲያን ተጀመረች

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው በኢየሩሳሌም ቆዩ። በዚያ የነበሩት አማኞች ያለ ማቋረጥ ለመጸለይ ይሰበሰቡ ነበር።

አይሁድ በያመቱ ከፋሲካ በኋላ ባሉት 50 ቀናት ጴንጤቆስጤ ተብሎ የሚጠራን ልዩ በዓል ያከብሩ ነበር። ጴንጤቆስጤ አይሁድ የመከር በዓልን የሚያከብሩበት ቀን ነበር። አይሁድ የጴንጤቆስጤን በዓል በአንድነት ለማክበር ከመላው ዓለም ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። በዚህ ዓመት፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ የጴንጤቆስጤ በዓል መጣ።

አማኞቹ ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው እያሉ፣ በድንገት የነበሩበት ቤት እንደ ብርቱ ነፋስ ባለው ድምፅ ተሞላ። ከዚያም በአማኞቹ ሁሉ ራስ ላይ የእሳት ነበልባል የሚመስል ነገር ታየ። ሁላቸውም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉና በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።

በኢየሩሳሌም የነበሩት ሰዎች ድምፁን በሰሙ ጊዜ፣ የሆነውን ነገር ለማየት ብዙ ሰዎች መጡ። አማኞቹ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች ሲያውጁ ሰዎቹ በሰሙ ጊዜ እነዚህን ነገሮች በገዛ ራሳቸው ቋንቋ በመስማታቸው ተደነቁ።

አንዳንዶቹ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ ሰክረዋል ብለው ወቀሱአቸው። ነገር ግን ጴጥሮስ ቆመና እንዲህ አላቸው፣ ‹‹እስቲ ስሙኝ! እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዮኤል ‹በመጨረሻው ቀን መንፈሴን አፈስሳለሁ!› ያለው ትንቢት በዚህ ተፈጽሟል።

‹‹የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እናንተ እንዳያችሁትና እንደምታውቁት ኢየሱስ በእግዚአብሔር ኃይል ብዙ ታላላቅ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደረገ ሰው ነው። ነገር ግን እናንተ ሰቀላችሁት!››

‹‹ኢየሱስ ቢሞትም እንኳ እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው። ይህም ‹ቅዱስህን በመቃብር መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም› የሚለው ትንቢት ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ሕያው አድርጎ ከሞት እንዳስነሣው እኛ ምስክሮች ነን።››

‹‹ኢየሱስ አሁን በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በክብር ተቀምጦአል። ደግሞም ኢየሱስ ልክ ተስፋ እንደ ሰጠው መንፈስ ቅዱስን ልኮአል። አሁን የምታዩአቸውንና የምትሰሙአቸውን ነገሮች ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነው ።

‹‹ይህንን ኢየሱስን ሰቀላችሁት። ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታና መሲሕ እንዳደረገው በእርግጥ እወቁ!››

ጴጥሮስን ይሰሙ የነበሩት ሰዎች በተናገራቸው ነገሮች በእጅጉ ተነኩ። ስለዚህ ጴጥሮስንና ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?›› ብለው ጠየቁአቸው።

ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ ‹‹እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ እያንዳንዳችሁ ንስሐ ግቡና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። ይህን ብታደርጉ እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ደግሞ ይሰጣችኋል።››

3000 የሚያህሉ ሰዎች ጴጥሮስ የተናገረውን አምነው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። እነርሱ ተጠምቀው በኢየሩሳሌም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሆኑ።፡

ደቀ መዛሙርቱ ያለ ማቋረጥ የሐዋርያትን ትምህርት ሰሙ፣ አብረው ጊዜ አሳለፉ፣ አብረው በሉ፣ አንዳቸው ለሌላኛው ጸለዩ። አብረው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፣ የነበራቸውንም ነገር ሁሉ እርስ በርስ ተካፈሉ። ሁሉም ሰው ያከብራቸው ነበር። በየዕለቱም ሌሎች ብዙ ሰዎች አማኞች ሆኑ።
_የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 2። _
44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ ሳሉ፣ ወደ ቤተ መቅደሱ ደጃፍ እንደ ቀረቡ፣ ገንዘብ ይለምን የነበረ ሽባ ሰው ዐዩ።

ጴጥሮስ ሽባውን ተመለከተውና፣ ‹‹የምሰጥህ ምንም ገንዘብ የለኝም። ያለኝን ግንእሰጥሃለሁ። በኢየሱስ ስም ተነሣና ተመላለስ!›› አለው።

ወዲያውኑ እግዚአብሔር ሽባውን ሰው ፈወሰው፣ እርሱም መራመድና መዝለል፣ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። በቤተ መቅደሱ አጥር ግቢ የነበሩት ሰዎችም ተደነቁ።

ሕዝቡም የተፈወሰውን ሰው ለማየት ፈጥነው ተሰበሰቡ፡፡ ጴጥሮስ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹ይህ ሰው ስለ ተፈወሰ ለምን ትደነቃላችሁ? በገዛ ኃይላችን ወይም በበጎነታችን አልፈወስነውም፡፡ ይህንን ሰው የፈወሰው የኢየሱስ ኃይልና ኢየሱስ የሚሰጠው እምነት ነው፡፡››

‹‹ኢየሱስን እንዲገድለው ለሮማው ገዥ የነገራችሁት እናንተ ናችሁ። የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ታደርጉት የነበረውን ነገር ባትረዱም እንኳ፣ መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት የተነገሩትን ትንቢቶች ለመፈጸም እግዚአብሔር በድርጊቶቻችሁ ተጠቀመ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ ይታጠብላችሁ ዘንድ አሁን ንስሐ ግቡና ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።››

የቤተ መቅደሱ መሪዎች ጴጥሮስና ዮሐንስ ይናገሩት በነበረው ነገር በጣም ተበሳጩ። ስለዚህ ያዙአቸውና እስር ቤት አስገቡአቸው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች የጴጥሮስን መልእክት አመኑ፣ በኢየሱስ ያመኑት ሰዎች ቊጥርም ወደ 5,000 ገደማ ዐደገ።

በማግስቱ፣ የአይሁድ መሪዎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሊቀ ካህናቱና ወደ ሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች አመጡአቸው። ጴጥሮስንና ዮሐንስን፣ ‹‹ይህንን ሽባ ሰው በምን ኃይል ፈወሳችሁት?›› ብለው ጠየቁአቸው።

ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ ‹‹ይህ ሰው በመሲሑ በኢየሱስ ኃይል ተፈውሶ በፊታችሁ ቆሞአል። እናንተ ኢየሱስን ሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን እንደ ገና ሕያው አድርጎ ከሙታን አስነሣው! እናንተ አልተቀበላችሁትም፣ ነገር ግን በኢየሱስ ኃይል ካልሆነ በቀር ሌላ የመዳን መንገድ የለም!››

ጴጥሮስና ዮሐንስ በጣም በድፍረት በመናገራቸው እነዚህ መሪዎች ደነገጡ፣ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን አይተው ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ አስታወሱ። ጴጥሮስንና ዮሐንስን ካስጠነቀቁአቸው በኋላ፣ እንዲሄዱ አሰናበቱአቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 3፡1-4፡22።
45. እስጢፋኖስ እና ፊሊጶስ

በጥንትዋ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት መሪዎች አንዱ እስጢፋኖስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። እርሱ መልካም ስም ያለውና መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላበት ሰው ነበር። እስጢፋኖስ ብዙ ተአምራትን ያደረገና ሰዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ በደንብ አስረድቶ ያሳምናቸው ነበር።

አንድ ቀን እስጢፋኖስ ስለ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ፣ በኢየሱስ ያላመኑ አንዳንድ አይሁዶች ከእስጢፋኖስ ጋር መከራከር ጀመሩ። በጣም ተቈጡና ስለ እስጢፋኖስ ለሃይማኖት መሪዎች ዋሽተው ተናገሩ። ‹‹ስለ ሙሴና ስለ እግዚአብሔር ክፉ ነገሮችን ሲናገር ሰምተነዋል!›› አሉ። ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ እስጢፋኖስን ያዙትና ወደ ሊቀ ካህናቱና ወደ ሌሎቹ የአይሁድ መሪዎች አምጥተው ሌሎች ተጨማሪ የሐሰት ምስክሮች ስለ እስጢፋኖስ ዋሽተው እንዲመሰክሩ አደረጉ።

ሊቀ ካህናቱ እስጢፋኖስን፣ ‹‹እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸውን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ እስጢፋኖስ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ዘመን ድረስ እግዚአብሔር ስላደረጋቸው ብዙ ታላላቅ ነገሮች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ በተከታታይ በእርሱ ላይ ስለ ማመፃቸው በማስታወስ መልስ ሰጠ፡፡ ከዚያም እንዲህ አለ፣ ‹‹እናንተ አንገተ ደንዳኖችና ዓመፀኞች ልክ ቅድመ አያቶቻችሁ እግዚአብሔርን እንደ ተቃወሙትና ነቢያቱን እንደ ገደሉ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፡፡ እናንተ ግን ከእነርሱ ይልቅ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፡፡ መሲሑን ገድላችኋል!››

የሃይማኖት መሪዎቹ ይህንን በሰሙ ጊዜ፣ በጣም ተናደው ጆሮአቸውን ደፈኑና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኹ። እስጢፋኖስን ከከተማይቱ ውጪ ጐተቱትና ሊገድሉት በድንጋይ ወገሩት።

እስጢፋኖስ በመሞት ላይ እያለ፣ ‹‹ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበላት›› ብሎ ጮኸ። ከዚያም በጉልበቱ ተንበረከከና፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ይህንን ኃጢአት አትቊጠርባቸው›› ብሎ እንደ ገና ጮኸ። ከዚያ በኋላ ሞተ።

ሳውል የተባለ አንድ ወጣት እስጢፋኖስን ከሚገድሉት ሰዎች ጋር ተስማምቶ በእርሱ ላይ ድንጋይ በሚወረውሩበት ጊዜ ልብሳቸውን ይጠብቅ ነበር። በዚያን ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች ማሳደድ ጀመሩ፣ ስለዚህ አማኞቹ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሸሹ። ነገር ግን ስደቱ ቢኖርም እንኳ፣ በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ስለ ኢየሱስ ሰበኩ።

ፊልጶስ የተባለ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በስደቱ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከሸሹት አማኞች አንዱ ነበር። ወደ ሰማርያ ሄዶ ስለ ኢየሱስ ሰበከና ብዙ ሰዎች ዳኑ። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ በምድረ በዳ ወዳለ አንድ መንገድ እንዲሄድ ለፊልጶስ ነገረው። ፊልጶስ በመንገዱ በመሄድ ላይ እያለ አንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን በሰረገላው ሲሄድ ዐየ። ወደዚህ ሰው ሄዶ እንዲያነጋግረው መንፈስ ቅዱስ ለፊልጶስ ነገረው።

ፊልጶስ ወደ ሰረገለው በቀረበ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊው ነቢዩ ኢሳይያስ ከጻፈው ውስጥ አንዱን ክፍል ሲያነብ ሰማ፡፡ ሰውዬው እንዲህ ብሎ ሲያነብ ነበር፣ ‹‹እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በፍርድ ተወሰደ፣ አላከበሩትምም፡፡ ከሕያዋን ምድር አስወገዱት፡፡››

ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን፣ ‹‹የምታነበውን ታስተውለዋለህን?›› ብሎ ጠየቀው። ኢትዮጵያዊውም፣ ‹‹አይደለም። የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳ እችላለሁ። እባክህን ናና ከጐኔ ተቀመጥ። ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ ሰው?›› ብሎ መለሰ።

ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ኢየሱስ መሆኑን ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው አብራራለት። ደግሞም ፊልጶስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሲያስረዳው ሌሎች የእግዚአብሔር ቃል ክፍሎችን ተጠቀመ።

ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ሲጓዝ ሳለ፣ ውሃ ወዳለበት ስፍራ ደረሱ፡፡ ኢትዮጵያዊውም፣ ‹‹እነሆ፣ በዚያ ቦታ ውሃ አለ! ልጠመቅን?›› አለ፡፡ ለነጂውም ሰረገላውን እንዲያቆመው ነገረው፡፡

ስለዚህ ወደ ውሃው ወረዱ፣ ፊልጶስም ኢትዮጵያዊውን አጠመቀው። ከውሃው ከወጡ በኋላ መንፈስ ቅደስ በድንገት ፊልጶስን ወደ ሌላ ስፍራ ወሰደው፤ ስለ ኢየሱስ ለሰዎች መናገሩንም ቀጠለ።

ኢትዮጵያዊው ኢየሱስን በማወቁ እየተደሰተ ወደ አገሩ ለመመለስ ጕዞውን ቀጠለ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 6፡8-8፡5፤ 8፡26-40።
46. ጳውሎስ ክርስቲያን ሆነ

ሳውል እስጢፋኖስ ሲገደል የገዳዮችን ልብስ ይጠብቅ የነበረ ወጣት ነው። እርሱ በኢየሱስ የማያምን ነበር፣ ስለዚህም አማኞችን ያሳድድ ነበር። ወንዶችንና ሴቶችን እየያዘ ወደ እስር ቤት ለመጨመር በኢየሩሳሌም ከቤት ወደ ቤት ይሄድ ነበር። ሊቀ ካህናቱ በዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ይይዝና ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ ወደ ደማስቆ ከተማ እንዲሄድ ለሳውል ፈቃድ ሰጡት።

ሳውል ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ እያለ፣ ከሰማይ ብሩህ ብርሃን በዙሪያው ሁሉ አበራ፣ እርሱም መሬት ላይ ወደቀ። ከዚያም፣ ‹‹ሳውል! ሳውል! ስለ ምን ታሳድደኛለህ?›› የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውል፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ?›› ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ ‹‹የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ›› ብሎ መለሰለት።

ሳውልም ከወደቀበት በተነሣ ጊዜ፣ ማየት ተሳነው። ወዳጆቹ ወደ ደማስቆ እየመሩ ወሰዱት። ሳውል ለሦስት ቀናት ምንም አልበላም ወይም አልጠጣም።

በደማስቆ ሐናንያ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። እግዚአብሔር ለሐናንያ፣ ‹‹ሳውል ወዳለበት ቤት ሂድ። እንደ ገና ያይ ዘንድ እጅህን ጫንበት›› አለው። ሐናንያ ግን፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው አማኞችን እንዴት እንዳሳደደ ሰምቼአለሁ›› አለ። እግዚአብሔር፣ ‹‹ሂድ! ለአይሁዶችና ለአሕዛብ ስሜን እንዲያውጅ መርጬዋለሁ። ስለ ስሜ ብዙ መከራ ይቀበላል›› አለው።

ስለዚህ ሐናንያ ወደ ሳውል ሄደ። እጆቹን ጫነበት፣ እንዲህም አለ፣ ‹‹ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የታየህ ኢየሱስ፣ እንደ ገና ታይና በመንፈስ ቅዱስ ትሞላ ዘንድ ወዳንተ ላከኝ።›› ሳውል ወዲያውኑ ማየት ቻለ፣ ሐናንያም አጠመቀው። ከዚያ በኋላ ሳውል ምግብ በላ፣ በረታም።

ሳውል ወዲያውኑ፣ ‹‹ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው!›› በማለት በደማስቆ ለነበሩ አይሁድ መስበክ ጀመረ። አይሁዶች አማኞችን ለማጥፋት የሞከረው ሰው አሁን ደግሞ በኢየሱስ በማመኑ ተደነቁ! ሳውል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለአይሁዶች አረጋገጠላቸው።

ከብዙ ቀናት በኋላ አይሁዶች ሳውልን ለመግደል ዐቀዱ። ይገድሉት ዘንድ በከተማይቱ በሮች የሚጠባበቁትን ሰዎች አቆሙ። ነገር ግን ሳውል ስለ ዕቅዱ ሰማ፣ ወዳጆቹም እንዲያመልጥ ረዱት። አንድ ሌሊት በቅርጫት አድርገው በከተማዪቱ ቅጥር አወረዱት። ሳውል ከደማስቆ ካመለጠ በኋላ ስለ ኢየሱሰ መስበኩን ቀጠለ።

ሳውል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፣ እነርሱ ግን ፈሩት። በዚያን ጊዜ በርናባስ የተባለ አማኝ ሳውልን ወደ ሐዋርያቱ ወሰደውና ሳውል በደማስቆ እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሳውልን ተቀበሉት።

በኢየሩሳሌም ከነበረው ስደት የሸሹ አንዳንድ አማኞች ወደ አንጾኪያ ድረስ ርቀው ሄዱና ስለ ኢየሱስ ሰበኩ፡፡ በአንጾኪያ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች አይሁዶች አልነበሩም፣ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙዎቻቸው በኢየሱስ አመኑ፡፡ በርናባስና ሳውል እነዚህን ዐዳዲስ አማኞች በተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ሊያስተምሯቸውና ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠናክሩ ወደዚያ ሄዱ፡፡ በኢየሱስ ያመኑት ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ‹‹ክርስቲያኖች›› ተባሉ፡፡

አንድ ቀን በአንጾኪያ የነበሩ ክርስቲያኖች እየጾሙና እየጸለዩ እያሉ መንፈስ ቅዱስ፣ ‹‹ለጠራኋቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ›› አላቸው። ስለዚህ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለበርናባስና ለሳውል ጸለዩላቸው፣ እጆቻቸውንም ጫኑባቸው። ከዚያም በሌሎች ብዙ ቦታዎች ስለ ኢየሱስ የምሥራች እንዲሰብኩ ላኩአቸው። በርባናስና ሳውል ከተለያዩ የሕዝብ ወገኖች የሆኑ ሰዎችን አስተማሩ፣ ብዙ ሰዎችም በኢየሱስ አመኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 8፡3፤ 9፡1-31፤ 11፡19-26፤ 13፡1-3።
47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ

ሳውል በሮማ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ሁሉ በሚጓዝበት ጊዜ፣ ‹‹ጳውሎስ›› የሚለውን ሮማዊ ስሙን ይጠቀም ጀመር። አንድ ቀን ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ስለ ኢየሱስ የምሥራች ሊያውጁ ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ሄዱ። ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ተሰበሰቡበት ከከተማይቱ ውጭ በወንዙ አጠገብ ወዳለ ስፍራ ሄዱ። በዚያ ነጋዴ የነበረች ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት አገኙ። እርስዋ እግዚአብሔርን የምትወድና የምታመልክ ሴት ነበረች።

ስለ ኢየሱስ የተነገረውን መልእክት እንድታምን እግዚአብሔር የልድያን ልብ ከፈተላት፤ እርስዋና ቤተ ሰብዋ ተጠመቁ፣ በቤትዋ እንዲቀመጡም ጳውሎስንና ሲላስን ጋበዘቻቸው፣ ስለዚህ እነርሱ ከእርስዋና ከቤተ ሰብዋ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ቆዩ።

ጳውሎስና ሲላስ ብዙ ጊዜ በጸሎት ስፍራ ከሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር። በየዕለቱ ወደዚያ ሲሄዱ ጋኔን የያዛት አንዲት የቤት ሠራተኛ ትከተላቸው ነበር። እርሷም በዚህ ጋኔን አማካይነት ስለ መጪው ጊዜ ለሰዎች ትተነብይላቸው ነበር፣ ስለዚህ በጥንቈላ ለጌቶችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝ ነበር።

የቤት ሠራተኛይቱም እነርሱ ሲዘዋወሩ እየተከተለቻቸው፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። ለእናንተ የመዳንን መንገድ ይነግሩአችኋል!›› በማለት መጮህዋን ቀጠለች። ይህንን ደጋግማ ስለ አደረገች ጳውሎስ ተበሳጨ።

በመጨረሻም አንድ ቀን ሠራተኛይቱ መጮኽ በጀመረች ጊዜ ጳውሎስ ወደ እርስዋ ዘወር አለና በእርስዋ የነበረውን ጋኔን፣ ‹‹በኢየሱስ ስም ከእርስዋ ውጣ›› አለው፡፡ ወዲያውኑ ጋኔኑ ለቀቃት፡፡

በዚህ የባሪያዪቱ ጌቶች በጣም ተቈጡ! ያለ ጋኔኑ ባሪያዪቱ ልጅ ስለ ሰዎች መጪ ጊዜ መናገር እንደማትችል ዐወቁ። ይህም ማለት ለሰዎች የወደፊቱን ነገር ልትነግራቸው ስለማትችል ለጌቶችዋ ገንዘብ አይከፍሉም ማለት ነው።

ስለዚህ የባሪያዪቱ ጌቶች ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ሮማ ባለ ሥልጣናት ወሰዱአቸው፣ እነርሱም ደብድበው ወደ እስር ቤት ጣሉአቸው።

የሮማ ወታደሮችም ጳውሎስንና ሲላስን በእስር ቤት ውስጠኛ ክፍል አሰሩአቸው፤ እግሮቻቸውንም ከግንድ ጋር አሰሩአቸው፡፡ ሆኖም ግን እኩለ ሌሊት ላይ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘመሩ፡፡

በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ! የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ ወለል ብለው ተከፈቱ፣ የእስረኞቹ ሁሉ ሰንሰለቶችም ረገፉ።

የእስር ቤቱ ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቃ፣ የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ መከፈታቸውን ባየ ጊዜ በጣም ደነገጠ! እስረኞቹ ሁሉ ያመለጡ መሰለው፣ ስለዚህ ራሱን ለመግደል ዐሰበ። (እስረኞቹ እንዲያመልጡ ካደረገ የሮማ ባለ ሥልጣናት እንደሚገድሉት ያውቅ ነበር።) ነገር ግን ጳውሎስ ዐየውና፣ ‹‹ተው! ራስህን አትጕዳ። እኛ ሁላችንም እዚህ አለን›› ብሎ ጮኸ።

የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ ጳውሎስና ሲላስ እየተንቀጠቀጠ መጣና፣ ‹‹እድን ዘንድ ምን ላድርግ?›› ብሎ ጠየቀ። ጳውሎስ፣ ‹‹በጌታ በኢየሱስ እመን፣ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ›› ብሎ መለሰለት። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው። ጳውሎስ በቤቱ ለነበሩት ሁሉ ስለ ኢየሱስ የምሥራች ሰበከላቸው።

የእስር ቤት ጠባቂውና መላው ቤተ ሰቡ በኢየሱስ አምነው ተጠመቁ። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ለጳውሎስና ለሲላስ ምግብ አቀረበላቸውና በአንድነት ደስ አላቸው።

በማግስቱ የከተማው መሪዎች ጳውሎስንና ሲላስን ከእስር ቤት ፈቱአቸውና ከፊልጵስዩስ እንዲሄዱ ጠየቁአቸው፡፡ ጳውሎስና ሲላስ ልድያንና አንዳንድ ሌሎች ወዳጆችን ጐበኙና ከተማይቱን ለቀው ሄዱ፡፡ የኢየሱስ የምሥራች ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ ቤተ ክርስቲያንም ማደግዋን ቀጠለች፡፡

ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኢየሱስ የምሥራች እየሰበኩና እያስተማሩ ወደ ብዙ ከተሞች ተጓዙ። ደግሞም በአብያተ ክርስቲያናቱ ላሉ አማኞች ሊያበረታቱአቸውና ሊያስተምሩአቸው ብዙ መልእክቶችን ጻፉላቸው። ከእነዚህ መልእክቶች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ሆኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 16፡11-40።
48. ኢየሱስ የተስፋው መሲሕ

እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረ ጊዜ ሁሉም ነገር ፍጹም ነበረ። ኃጢአት አልነበረም። አዳምና ሔዋን እርስ በርሳቸው ይዋደዱ ነበር፣ እግዚአብሔርንም ይወዱት ነበር። በሽታ ወይም ሞት አልነበረም። እግዚአብሔር የፈለገው ዓለም እንደዚህ እንድትሆን ነበር።

ሰይጣን በገነት ሔዋንን ያስት ዘንድ በእባቡ በኩል ተናገረ። በዚያን ጊዜ እርስዋና አዳም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። እነርሱ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት በምድር ያለ ሰው ሁሉ ይታመማል፤ ይሞታልም።

አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ከዚህም የበለጠ ክፉ ነገር ሆነ። እነርሱ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆኑ። ከዚህ የተነሣ ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ሁሉም ሰው በኃጢአተኛ ባሕርይ ተወልዶአል፤ ደግሞም የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የነበረው ግንኙነት በኃጢአት ምክንያት ተቋረጠ። ነገር ግን እግዚአብሔር ያንን ግንኙነት የመመለስ ዕቅድ ነበረው።

ከሔዋን ዝርያዎች አንዱ የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥ፣ ሰይጣንም ሰኰናውን እንዲያቈስል እግዚአብሔር ተስፋ ሰጠ። ይህም ሰይጣን መሲሑን ይገድላል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ገና ከሞት ያስነሣዋል ማለት ነው፣ ከዚያም መሲሑ የሰይጣንን ራስ ለዘላለም ይቀጠቅጠዋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር መሲሑ ኢየሱስ መሆኑን ገለጠ።

እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ በጥፋት ውሃ ባጠፋ ጊዜ፣ በእርሱ ያመኑትን ሰዎች ለማዳን መርከብ አቀረበ። ልክ እንደዚሁ ሰው ሁሉ በኃጢአቱ ምክንያት መጥፋት ይገባው ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ለማዳን ኢየሱስን ሰጠ።

ለብዙ መቶ ዓመታት ካህናት ሰዎች ለኃጢአታቸው የሚገባቸውን ቅጣት መቀበል እንደሚገባቸው ለማሳየት ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ያለ ማቋረጥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ነገር ግን እነዚያ መሥዋዕቶች ኃጢአታቸውን ሊያስወግዱ አልቻሉም። ኢየሱስ ታላቁ ሊቀ ካህናት ነው። ከሌሎች ካህናት በተለየ ሁኔታ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ኃጢአት ማስወገድ የሚችል ብቸኛ መሥዋዕት አድርጎ ራሱን አቀረበ። ኢየሱስ ማንኛውም ሰው የሠራውን የእያንዳንዱን ኃጢአት ቅጣት ስለ ወሰደ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው።

እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ‹‹የምድር ሕዝብ ወገኖች ሁሉ በአንተ ዘር ይባረካሉ›› ብሎ ነገረው። ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ነው። በእርሱ በኩል የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ተባርከዋል፣ ምክንያቱም በኢየሱስ የሚያምን ሰው ሁሉ ከኃጢአት ድኖአል፣ እንዲሁም የአብርሃም መንፈሳዊ ልጅ ይሆናል።

ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ለአብርሃም በነገረው ጊዜ፣ እግዚአብሔር በልጁ በይስሐቅ ፈንታ የመሥዋዕት በግ አቀረበ። እኛ ሁላችንም በኃጢአታችን መሞት ይገባናል! ነገር ግን እግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ በእኛ ቦታ እንዲሞት የእግዚአብሔር በግ የሆነውን ኢየሱስን ሰጠ።

እግዚአብሔር በግብፅ ላይ የመጨረሻውን መቅሠፍት በላከ ጊዜ እንከን የሌለበት ጠቦት እንዲያርዱና ደሙን በበሩ መቃንና ጉበን ላይ እንዲረጩት ለእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች ሁሉ ተናገረ። እግዚአብሔርም ደሙን ባየ ጊዜ ቤቶቹን አልፎ ሄደ፤ በኵር ልጆቻቸውንም አልገደለም። ይህ ታሪካዊ ድርጊት ፋሲካ ተብሎአል።

ኢየሱስ የፋሲካ በጋችን ነው። እርሱ ፍጹምና ምንም ኃጢአት የሌለብት የእግዚእብሔር በግ ነው፤ በፋሲካ በዓል ጊዜም ተገደለ። ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ጊዜ፣ የኢየሱስ ደም ለዚያ ሰው ኃጢአት ክፍያ ነው፣ የእግዚአብሔር ቅጣትም ከዚያ ሰው ላይ ያልፋል።

እግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቡ ከነበሩት ከእስራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ነገር ግን አሁን እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው የሚሆን ዐዲስ ቃል ኪዳን አድርጎአል። በዚህ ዐዲስ ቃል ኪዳን ምክንያት ከማንም ሕዝብ ወገን የሆነ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆን ይችላል።

ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ያወጀ ታላቅ ነቢይ ነበረ። ኢየሱስ ግን ከሁሉም የላቀ ነቢይ ነው። እርሱ አምላክ ነው፣ ስለዚህ እርሱ ያደረገውና የተናገረው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራና የእግዚአብሔር ቃል ነው።

እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት ከትውልዱ አንዱ ንጉሥ ሆኖ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ለዘላለም እንደሚገዛ ተስፋ ሰጠው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና መሲሑ ስለሆነ፣ ለዘላለም መግዛት የሚችል ልዩ የዳዊት ዘር እርሱ ነው።

ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ነበር፣ ኢየሱስ ግን የፍጥረት ዓለም ሁሉ ንጉሥ ነው! ተመልሶ ይመጣና በፍትሕና በሰላም መንግሥቱን ለዘላለም ይገዛል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 1-3፤ 6፤ 14፤ 22፤ ዘጸአት 12፣ 20፤ 2ኛ ሳሙኤል 7፤ ዕብራውያን 3፡1-6፤ 4፡14-5፡10፤ 7፡1-8፡13፤ 9፡11-10፡18፤ ራእይ 21።
49. ዐዲሱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን

አንድ መልአክ ማርያም ለተባለች ድንግል የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትወልድ ነገራት፡፡ ስለዚህ እርስዋ ገና ድንግል እያለች መንፈስ ቅዱስ ጸለለላትና አረገዘች። ወንድ ልጅም ወለደችና ስሙን ኢየሱስ ብላ ጠራችው፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ አምላክም ሰውም ሆነ፡፡

ኢየሱስ የእግዚብሔር ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ በውሃ ላይ ተራመደ፣ ማዕበልን ጸጥ አደረገ፣ ብዙ በሽተኞችን ፈወሰ፣ አጋንንትን አወጣ፣ ሙታንን ሕያው አድርጎ አስነሣ፣ እንዲሁም አምስት እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ ከ5,000 ለበለጡ ሰዎች እንዲበቃ አደረገ፡፡

ደግሞም ኢየሱስ ታላቅ መምህር ነው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነም በሥልጣን ተናገረ፡፡ ራሳችሁን እንደምትወዱ ሌሎች ሰዎችንም ውደዱ ብሎ አስተማረ፡፡

ደግደግሞም እርሱ ሀብታችሁን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ከምትወዱት አብልጣችሁ እግዚአብሔርን መውደድ አለባችሁ ብሎ አስተማረ፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለም ካለ ከማንኛውም ነገር ይልቅ የከበረች ነች አለ፡፡ ለማንኛውም ሰው እጅግ በጣም አስፈላጊው ነገር የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ መሆን ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ከኃጢአታችሁ መንጻት አለባችሁ፡፡

ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች እርሱን ተቀብለውት እንደሚድኑ፣ ሌሎች ግን እንደማይቀበሉት አስተማረ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደ መልካም መሬት ናቸው አለ፡፡ የኢየሱስን የምሥራች ተቀብለው ይድናሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል እንደማይገባበትና ምንም ፍሬ እንደማያፈራ መንገድ ዳር እንዳለ መሬት ናቸው፡፡ እነዚያ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን መልእክት የማይቀበሉና ወደ መንግሥቱ የማይገቡ ናቸው፡፡

ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በጣም እንደሚወድ አስተማረ፡፡ ይቅር ሊላቸውና ልጆቹም ሊያደርጋቸው ይፈልጋል፡፡

ደግሞም ኢየሱስ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንደሚጠላ ነግሮናል፡፡ አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ፣ ኃጢአቱ ዝርያዎቻቸውን ሁሉ አበላሸ፡፡ ከዚህ የተነሣ በዓለም ላይ ያለ ሁሉም ሰው ኃጢአት ሠርቶአል፤ ከእግዚአብሔርም ተለይቶአል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል፡፡

ነገር ግን በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል፡፡

በኃጢአታችሁ ምክንያት በደለኞች ናችሁና መሞት ይገባችኋል፡፡ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ መቈጣት ነበረበት፣ ነገር ግን ቊጣውን በእናንተ ላይ በማድረግ ፈንታ በኢየሱስ ላይ አፈሰሰው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፣ የእናንተን ቅጣት ተቀበለ፡፡፡

ኢየሱስ በፍጹም ኃጢአት አላደረገም፣ ነገር ግን የእናንተን ኃጢአትና በዓለም ያለውን የእያንዳንዱን ሰው ኃጢአት ለማስወገድ መቀጣትንና ፍጹም መሥዋዕት ሆኖ መሞትን መረጠ፡፡ ኢየሱስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ ኢየሱስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ስላቀረበ እግዚአብሔር ማንኛውንም ኃጢአት፣ አስከፊ የሆነውን ኃጢአት እንኳ ይቅር ማለት ይችላል፡፡

መልካም ሥራዎች ሊያድኑአችሁ አይችሉም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲኖራችሁ ልታደርጉ የምትችሉበት ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ብቻ ኃጢአታችሁን ሊያጥብ ይችላል፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ በእናንተ ፈንታ በመስቀል ላይ መሞቱን እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ብቻ ማመን አለባችሁ፡፡

እግዚአብሔር በኢየሱስ የሚያምነውንና ጌታው አድርጎ የሚቀበለውን ማንኛውንም ሰው ያድናል፡፡ ነገር ግን በእርሱ የማያምነውን ማንኛውንም ሰው አያድንም። ባለ ጠጎች ብትሆኑ ወይም ድሆች፣ ወንድ ወይም ሴት፣ ሽማግሌ ወይም ወጣት ብትሆኑ፣ ወይም የትም ብትኖሩ እግዚአብሔር ይወዳችኋል፤ በኢየሱስ እንድታምኑና ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖራችሁም ይፈልጋል፡፡

ኢየሱስ በእርሱ እንድታምኑና እንድትጠመቁ ይጋብዛችኋል፡፡ ኢየሱስ መሲሕና ብቸኛው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምናላችሁ? ኃጢአተኞች መሆናችሁንና እግዚአብሔርም እናንተን መቅጣት እንዳለበት ታምናላችሁ? ኢየሱስ ኃጢአታችሁን ለማስወገድ በመስቀል ላይ መሞቱን ታምናላችሁ?

በኢየሱስና እርሱ ለእናንተ በሠራው ሥራ ብታምኑ፣ እናንተ ክርስቲያኖች ናችሁ! እግዚአብሔርም ከሰይጣንና ከጨለማ መንግሥት አውጥቶአችሁ በእግዚአብሔር የብርሃን መንግሥት ውስጥም አድርጎአችኋል፡፡ እግዚአብሔር ታደርጉት የነበረውን አሮጌውንና ኃጢአተኛውን መንገዳችሁን አስወግዶ ዐዲስና የጽድቅ መንገድ እንድትኖሩ ዐዲስ ሕይወትን ሰጥቶአችኋል፡፡

እናንተ ክርስቲያኖች ከሆናችሁ፣ ኢየሱስ በሠራው ሥራ ምክንያት እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር ብሏችኋል። አሁን እግዚአብሔር የእርሱ ጠላቶች ሳትሆኑ የቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ ይቈጥራችኋል።

እናንተ የእግዚአብሔር ወዳጆችና የጌታ ኢየሱስ አገልጋዮች ከሆናችሁ፣ ኢየሱስ ለሚያስተምራችሁ ነገር ትታዘዛላችሁ። ክርስቲያኖች ብትሆኑም እንኳ፣ አሁንም ኃጢአት ለመሥራት ትፈተናላችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር የታመነ ነውና ‹‹ኃጢአታችሁን ብትናዘዙ ይቅር እላችኋለሁ›› ይላል። ኃጢአትን የምትቃወሙበትንም ኃይል ይሰጣችኋል።

እግዚአብሔር እንድትጸልዩ፣ ቃሉን እንድታጠኑ፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር እንድታመልኩ፣ ያደረገላችሁንም ለሌሎች እንድትነግሩ ይጠይቃችኋል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ይረዱአችኋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሮሜ 3፡21-26፤ 5፡1-11፤ ዮሐንስ 3፡16፤ ማርቆስ 16፡16፤ ቈላስይስ 1፡13-14፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17-21፤ 1ኛ ዮሐንስ 1፡5-10፡፡
50. ኢየሱስ ይመለሳል

ለ2,000 ዓመታት ያህል በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ መሲሑ ኢየሱስ የሚነገረውን የምሥራች እየሰሙ ቈይተዋል። ቤተ ክርስቲያን እያደገች ኖራለች። ኢየሱስ በዓለም ፍጻሜ እንደሚመለስ ተስፋ ሰጥቶአል። እርሱ ገና እስካሁን ባይመለስም እንኳ፣ የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ይመጣል።

እግዚአብሔር የኢየሱስን መመለስ እየተጠባበቅን፣ ቅዱስ በሆነና እርሱን በሚያስከብረው መንገድ እንድንኖር ይፈልጋል። ደግሞም ስለ መንግሥቱ ለሌሎች እንድንናገር ይፈልጋል። ኢየሱስ በምድር ላይ ይኖር በነበረበት ጊዜ ሲያስተምር፣ ‹‹ደቀ መዛሙርቴ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች በዓለም ሁሉ በሁሉም ስፍራ ላሉ ሰዎች ይሰብካሉ፣ በዚያን ጊዜ ፍጻሜ ይመጣል›› ብሏል።

ብዙ የሕዝብ ወገኖች አሁንም ስለ ኢየሱስ አልሰሙም። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት፣ የምሥራቹን ላልሰሙት ሰዎች እንዲያውጁ ለክርስቲያኖች ነገራቸው። ‹‹ሂዱና የሕዝብ ወገኖችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው!›› አለ። ደግሞም ‹‹መከሩም ደርሶአል!›› አለ።

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹‹አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም። ልክ የዚህ ዓለም ባለ ሥልጣናት እኔን እንደ ጠሉኝ፤ እናንተንም በእኔ ምክንያት ያሠቃዩአችሁና ይገድሉአችኋል። ምንም እንኳ በዚህ ዓለም መከራ ብትቀበሉም፣ አይዞአችሁ ምክንያቱም እኔ ይህን ዓለም የሚገዛውን ሰይጣንን አሸንፌዋለሁ። እናንተ በእኔ አምናችሁ እስከ መጨረሻ ብትጸኑ፣ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ያድናችኋል!››

ኢየሱስ የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ፣ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ነገር ለማብራራት ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ‹‹አንድ ሰው በእርሻው መልካም ዘርን ዘራ። ተኝቶ እያለ ጠላቱ መጣና በስንዴው ላይ የአረም ዘር ዘራበትና ሄደ።››

‹‹የተዘራው ስንዴ በበቀለ ጊዜ፣ የሰውዬው አገልጋዮች፣ ‹ጌታው፣ በዚያ እርሻ መልካም ዘር ዘርተህ ነበር። ታዲያ በውስጡ ለምንድን ነው አረም ያለበት?› ብለው ጠየቁት፣ ጌታውም፣ ‹የዘራው ጠላት መሆን አለበት››› ብሎ መለሰላቸው።

‹‹አገልጋዮቹ ለጌታቸው፣ ‹አረሙን እንንቀለውን?› ብለው ጠየቁት። ጌታቸው እንዲህ አለ፣ ‹አይደለም። ይህንን ብታደርጉ ስንዴውንም ትነቅሉታላችሁ። እስከ መከር ድረስ ይቆዩ፤ በዚያን ጊዜ መላእክትን እልካለሁ። እነርሱም አረሙን ሰብስበው ያቃጥላሉ። ስንዴውን ግን በጎተራዬ ያከማቻሉ››› አላቸው።

ደቀ መዛሙርቱ የምሳሌው ትርጕም አልገባቸውም፣ ስለዚህ እንዲያብራራላቸው ኢየሱስን ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹‹መልካሙን ዘር የዘራው ሰው መሲሑን ይወክላል። እርሻው ዓለምን ይወክላል። መልካሙ ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሰዎች ይወክላል።››

‹‹አረሙ ከክፉው ወገን የሆኑ ሰዎችን ይወክላል። አረሙን የዘራው ጠላት ዲያብሎስን ይወክላል። መከሩ የዓለምን ፍጻሜ ይወክላል፣ አጫጆቹም የእግዚአብሔርን መላእክት ይወክላሉ።

‹‹በዓለም ፍጻሜ፣ መላእክት የዲያብሎስ ወገኖች የሆኑ ሰዎችን ሁሉ በአንድ ላይ ይሰበስቡና ወደሚንቀለቀል እሳት ይጥሉአቸዋል፣ በዚያም ይጮኻሉ፤ አስከፊ በሆነ ሥቃይም ጥርሶቻቸውን ያፋጫሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው በእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፡፡››

ደግሞም ኢየሱስ ልክ ከዓለም ፍጻሜ በፊት ወደ ምድር እንደሚመለስ ተናገረ። በሄደበት አኳኋን ተመልሶ ይመጣል፣ ይኸውም፣ አካላዊ ሰውነት ይኖረዋል፣ በሰማይ ደመናም ይመጣል። ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ እያንዳንዱ በክርስቶስ አምኖ የሞተ ክርስቲያን ከሙታን ይነሣና በሰማይ ላይ ይገናኘዋል።

በዚያን ጊዜ ገና በሕይወት ያሉ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ይነጠቁና ከሙታን ከተነሡ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ይቀላቀላሉ። በዚያ ሁላቸውም ከኢየሱስ ጋር ይሆናሉ። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር ፍጹም በሆነ ሰላምና አንድነት ለዘላለም ይኖራል።

ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ አክሊል ለመስጠት ተስፋ ሰጥቶአል። እነርሱ ፍጹም በሆነ ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም ይኖራሉ ይነግሣሉም።

ነገር ግን እግዚአብሔር በኢየሱስ በማያምኑ ሁሉ ላይ ይፈርዳል። ለዘላለም ወደሚያለቅሱበትና በሥቃይ ጥርሶቻቸውን ወደሚያፏጩበት ወደ ገሃነም እሳት ይጥላቸዋል። ከቶ የማይጠፋ እሳት ባለማቋረጥ ያቃጥላቸዋል።

ኢየሱስ በሚመለሰበት ጊዜ፣ ሰይጣንና መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ያጠፋቸዋል። ሰይጣንን ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ እርሱን ለመከተል ከመረጡት ሁሉ ጋር ለዘላለም ወደሚቃጠሉበት ወደ ገሃነም ይጥለዋል።

አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙና ኃጢአትን ወደዚህ ዓለም ስላመጡ፣ እግዚአብሔር ዓለምን ረገማት፤ ሊያጠፋትም ወሰነ። ነገር ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ፍጹም የሆነ ዐዲስ ሰማይና ዐዲስ ምድር ይፈጥራል።

ኢየሱስና ሕዝቡ በዐዲሲቱ ምድር ይኖራሉ፣ ኢየሱስ በሁሉም ነገር ላይ ለዘላለም ይነግሣል፡፡ እርሱ እንባን ሁሉ ያብሳል፣ ከእንግዲህ ወዲያ ሥቃይ፣ ሐዘን፣ ልቅሶ፣ ክፋት፣ ሕመም፣ ወይም ሞት አይኖርም፡፡ ኢየሱስ መንግሥቱን በሰላምና በፍትሕ ይገዛል፣ ለዘላለምም ከሕዝቡ ጋር ይሆናል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 24፡14፤ 28፡18፤ ዮሐንስ 15፡20፤ 16፡33፤ ራእይ 2፡10፤ ማቴዎስ 13፡24-30፤ 36-42፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-5፡11፤ ያዕቆብ 1፡12፤ ማቴዎስ 22፡13፤ ራእይ 20፡10፤ 21፡1-22፡21፡፡