17. እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

ሳኦል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ነበር፡፡ እርሱ ልክ ሕዝቡ እንደ ፈለጉት ረጅምና መልከ መልካም ነበር፡፡ ሳኦል እስራኤልን በገዛባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ጥሩ ንጉሥ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለእግዚአብሔር ያልታዘዘ ክፉ ሰው ሆነ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ቀን በሳኦል ቦታ ንጉሥ የሚሆን የተለየ ሰው መረጠ፡፡

እግዚአብሔር ከሳኦል በኋላ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊት የተባለውን እስራኤላዊ ወጣት መረጠ፡፡ ዳዊት ከቤተ ልሔም ከተማ የሆነ የበጎች እረኛ ነበር፡፡ ዳዊት በተለያዩ ጊዜያት የአባቱን በጎች ሲጠብቅ፣ በጎቹን ለማጥቃት የመጡትን አንበሳና ድብ ገድሎ ነበር፡፡ ዳዊት በእግዚአብሔር የሚያምንና ለእርሱም የሚታዘዝ ትሑትና ጻድቅ ሰው ነበር፡፡

ዳዊት ታላቅ ወታደርና መሪ ሆነ፡፡ ዳዊት ገና ወጣት በነበረ ጊዜ ጎልያድ ተብሎ ከሚጠራ ግዙፍ ሰው ጋር ተዋጋ፡፡ ጎልያድ የሠለጠነ ወታደር፣ በጣም ብርቱ፣ እንዲሁም ቁመቱ ከሞላ ጎደል ሦስት ሜትር ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጎልያድን ገድሎ እስራኤልን እንዲያድን ዳዊትን ረዳው፡፡ ከዚያ በኋላ ዳዊት በሕዝቡ የተመሰገነባቸውን፣ በእስራኤል ጠላቶች ላይ ብዙ ድሎችን አገኘ፡፡

ሳኦል ሕዝቡ ለዳዊት በነበራቸው ፍቅር ቀና፡፡ ሳኦል ብዙ ጊዜ ዳዊትን ሊገድለው ሞከረ፣ ስለዚህ ዳዊት ከሳኦል ተሸሸገ፡፡ አንድ ቀን ሳኦል ይገድለው ዘንድ ዳዊትን እየፈለገው ነበር፡፡ ሳኦል ዳዊት ከእርሱ ተሸሽጎበት ወደ ነበረው ዋሻ ሄደ፣ ነገር ግን ሳኦል አላየውም ነበር፡፡ ዳዊትም ወደ ሳኦል በጣም ተጠግቶ ነበርና ሊገድለው ይችል ነበር፣ ነገር ግን አልገደለውም፡፡ በዚህ ፈንታ ዳዊት ንጉሥ ለመሆን እንዳልገደለው ለሳኦል ለማረጋገጥ የሳኦልን ልብስ ዘርፍ ቈረጠ፡፡

በመጨረሻ፣ ሳኦል በጦርነት ሞተ፣ ዳዊትም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ ዳዊት ጥሩ ንጉሥ ነበረ፣ ሕዝቡም ወደዱት፡፡ እግዚአብሔር ዳዊትን ባረከው፣ ስኬታማም አደረገው፡፡ ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን ተዋጋ፣ የእስራኤልን ጠላቶች እንዲያሸንፍም እግዚአብሔር ረዳው፡፡ ዳዊት ኢየሩሳሌምን አሸንፎ ያዘና ዋና ከተማው አደረጋት፡፡ በዳዊት ንግሥና ጊዜ፣ እስራኤል ኃያልና ባለ ጠጋ ሆነች፡፡

ዳዊት እስራኤላውያን ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትና ለእርሱ መሥዋዕቶችን የሚያቀርቡበት ቤተ መቅደስ ለመሥራት ፈለገ፡፡ ሕዝቡ ለ400 ዓመት ገደማ ሙሴ በሠራው የመገናኛ ድንኳን እግዚአብሔርን ያመልኩና መሥዋዕቶችን ያቀርቡለት ነበር፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ የሚል መልዕክት በነቢዩ ናታን በኩል ወደ ዳዊት ላከው፣ ‹‹አንተ የጦርነት ሰው ስለ ሆንክ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ አትሠራልኝም፡፡ ልጅህ ይሠራዋል፡፡ ነገር ግን አንተን በእጅጉ እባርክሃለሁ፡፡ ከዝርያዎችህ አንዱ በሕዝቤ ላይ ንጉሥ ሆኖ ለዘላለም ይገዛል!›› ለዘላለም የሚገዛው ብቸኛው የዳዊት ዝርያ፣ መሲሑ ነው፡፡ መሲሑ የዓለምን ሕዝቦች ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ምርጥ ነው፡፡

ዳዊት እነዚህን ቃሎች በሰማ ጊዜ፣ ይህንን ታላቅ ክብርና ብዙ በረከቶችን ሊሰጠው ቃል ስለ ገባለት ወዲያውኑ እግዚአብሔርን አመሰገነ አወደሰም፡፡ ዳዊት እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች መቼ እንደሚያደርግ ግን አላወቀም፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን መሲሑ እስከሚመጣ ረዘም ላለ ጊዜ፣ ከሞላ ጐደል 1000 ዓመታት መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

ዳዊት በፍትሕና በታማኝነት ለብዙ ዓመታት ገዛ፣ እግዚአብሔርም ባረከው። ይሁን እንጂ፣ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ በእግዚአብሔር ላይ ክፉኛ ኃጢአት ሠራ።

አንድ ቀን የዳዊት ወታደሮች በሙሉ ከቤታቸው ርቀው ጦርነት በሚዋጉበት ጊዜ፣ እርሱ ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ ዐየ። ስምዋ ቤርሳቤህ ነበር።

ዳዊት ፊቱን ከሷ በማዞር ፈንታ፣ ወደ እርሱ እንዲያመጣት ሰው ላከ፡፡ ከእርስዋ ጋር ተኛና ወደ ቤቷ መልሶ ላካት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤርሳቤህ አርግዣለሁ ብላ ወደ ዳዊት መልእክት ላከች፡፡

ኦርዮ ተብሎ የሚጠራው የቤርሳቤህ ባል ከዳዊት ምርጥ ወታደሮች አንዱ ነበር፡፡ ዳዊት ኦርዮን ከጦርነቱ ቦታ ጠራውና ከሚስቱ ጋር እንዲሆን ነገረው፡፡ ነገር ግን ኦርዮ የቀሩት ወታደሮች በጦርነት ላይ እያሉ ወደ ቤት አልሄድም አለ፡፡ ስለዚህ ዳዊት ኦርዮንን ወደ ጦርነቱ መልሶ ላከውና ይገደል ዘንድ ጠላት እጅግ በበረታበት ቦታ እንዲያሰልፈው ለሠራዊቱ ዋና አዛዥ ነገረው፡፡

ኦርዮ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት፡፡ በኋላ እርስዋ ለዳዊት ወንድ ልጅን ወለደችለት፡፡ እግዚአብሔር ዳዊት ስላደረገው ነገር በጣም ተቈጣ፣ ኃጢአቱ እንዴት ክፉ እንደ ነበረ ለዳዊት እንዲነግረውም እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ላከው፡፡ ዳዊት ኃጢአቱን ተናዘዘና እግዚአብሔር ይቅር አለው፡፡ ዳዊት በቀረው የሕይወቱ ዘመን በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳ፣ እግዚአብሔርን ተከተለ፤ ታዘዘውም፡፡

ነገር ግን ዳዊት ለሠራው ኃጢአት ቅጣት እንዲሆን ሆኖ የተወለደው ልጁ ሞተበት፡፡ ደግሞም በቀረው የሕይወቱ ዘመን በዳዊት ቤተ ሰብ ውጊያ ነበረ፣ የዳዊት ኃይልም በእጅጉ ተዳከመ፡፡ ዳዊት ለእግዚአብሔር ያልታመነ ቢሆንም እንኳ፣ እግዚአብሔር አሁንም ለተስፋዎቹ የታመነ ነበረ፡፡ በኋላ ዳዊትና ቤርሳቤህ ሌላ ወንድ ልጅ ወለዱ፣ ስሙንም ሰሎሞን አሉት፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ሳሙኤል 10፡15-19፤ 24፤ 31፤ 2ኛ ሳሙኤል 5፤ 7፤ 11-12፡፡