43. ቤተ ክርስቲያን ተጀመረች

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው በኢየሩሳሌም ቆዩ። በዚያ የነበሩት አማኞች ያለ ማቋረጥ ለመጸለይ ይሰበሰቡ ነበር።

አይሁድ በያመቱ ከፋሲካ በኋላ ባሉት 50 ቀናት ጴንጤቆስጤ ተብሎ የሚጠራን ልዩ በዓል ያከብሩ ነበር። ጴንጤቆስጤ አይሁድ የመከር በዓልን የሚያከብሩበት ቀን ነበር። አይሁድ የጴንጤቆስጤን በዓል በአንድነት ለማክበር ከመላው ዓለም ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። በዚህ ዓመት፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ የጴንጤቆስጤ በዓል መጣ።

አማኞቹ ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው እያሉ፣ በድንገት የነበሩበት ቤት እንደ ብርቱ ነፋስ ባለው ድምፅ ተሞላ። ከዚያም በአማኞቹ ሁሉ ራስ ላይ የእሳት ነበልባል የሚመስል ነገር ታየ። ሁላቸውም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉና በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።

በኢየሩሳሌም የነበሩት ሰዎች ድምፁን በሰሙ ጊዜ፣ የሆነውን ነገር ለማየት ብዙ ሰዎች መጡ። አማኞቹ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች ሲያውጁ ሰዎቹ በሰሙ ጊዜ እነዚህን ነገሮች በገዛ ራሳቸው ቋንቋ በመስማታቸው ተደነቁ።

አንዳንዶቹ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ ሰክረዋል ብለው ወቀሱአቸው። ነገር ግን ጴጥሮስ ቆመና እንዲህ አላቸው፣ ‹‹እስቲ ስሙኝ! እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዮኤል ‹በመጨረሻው ቀን መንፈሴን አፈስሳለሁ!› ያለው ትንቢት በዚህ ተፈጽሟል።

‹‹የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እናንተ እንዳያችሁትና እንደምታውቁት ኢየሱስ በእግዚአብሔር ኃይል ብዙ ታላላቅ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደረገ ሰው ነው። ነገር ግን እናንተ ሰቀላችሁት!››

‹‹ኢየሱስ ቢሞትም እንኳ እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው። ይህም ‹ቅዱስህን በመቃብር መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም› የሚለው ትንቢት ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ሕያው አድርጎ ከሞት እንዳስነሣው እኛ ምስክሮች ነን።››

‹‹ኢየሱስ አሁን በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በክብር ተቀምጦአል። ደግሞም ኢየሱስ ልክ ተስፋ እንደ ሰጠው መንፈስ ቅዱስን ልኮአል። አሁን የምታዩአቸውንና የምትሰሙአቸውን ነገሮች ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነው ።

‹‹ይህንን ኢየሱስን ሰቀላችሁት። ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታና መሲሕ እንዳደረገው በእርግጥ እወቁ!››

ጴጥሮስን ይሰሙ የነበሩት ሰዎች በተናገራቸው ነገሮች በእጅጉ ተነኩ። ስለዚህ ጴጥሮስንና ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?›› ብለው ጠየቁአቸው።

ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ ‹‹እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ እያንዳንዳችሁ ንስሐ ግቡና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። ይህን ብታደርጉ እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ደግሞ ይሰጣችኋል።››

3000 የሚያህሉ ሰዎች ጴጥሮስ የተናገረውን አምነው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። እነርሱ ተጠምቀው በኢየሩሳሌም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሆኑ።፡

ደቀ መዛሙርቱ ያለ ማቋረጥ የሐዋርያትን ትምህርት ሰሙ፣ አብረው ጊዜ አሳለፉ፣ አብረው በሉ፣ አንዳቸው ለሌላኛው ጸለዩ። አብረው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፣ የነበራቸውንም ነገር ሁሉ እርስ በርስ ተካፈሉ። ሁሉም ሰው ያከብራቸው ነበር። በየዕለቱም ሌሎች ብዙ ሰዎች አማኞች ሆኑ።
_የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 2። _