47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ

ሳውል በሮማ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ሁሉ በሚጓዝበት ጊዜ፣ ‹‹ጳውሎስ›› የሚለውን ሮማዊ ስሙን ይጠቀም ጀመር። አንድ ቀን ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ስለ ኢየሱስ የምሥራች ሊያውጁ ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ሄዱ። ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ተሰበሰቡበት ከከተማይቱ ውጭ በወንዙ አጠገብ ወዳለ ስፍራ ሄዱ። በዚያ ነጋዴ የነበረች ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት አገኙ። እርስዋ እግዚአብሔርን የምትወድና የምታመልክ ሴት ነበረች።

ስለ ኢየሱስ የተነገረውን መልእክት እንድታምን እግዚአብሔር የልድያን ልብ ከፈተላት፤ እርስዋና ቤተ ሰብዋ ተጠመቁ፣ በቤትዋ እንዲቀመጡም ጳውሎስንና ሲላስን ጋበዘቻቸው፣ ስለዚህ እነርሱ ከእርስዋና ከቤተ ሰብዋ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ቆዩ።

ጳውሎስና ሲላስ ብዙ ጊዜ በጸሎት ስፍራ ከሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር። በየዕለቱ ወደዚያ ሲሄዱ ጋኔን የያዛት አንዲት የቤት ሠራተኛ ትከተላቸው ነበር። እርሷም በዚህ ጋኔን አማካይነት ስለ መጪው ጊዜ ለሰዎች ትተነብይላቸው ነበር፣ ስለዚህ በጥንቈላ ለጌቶችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝ ነበር።

የቤት ሠራተኛይቱም እነርሱ ሲዘዋወሩ እየተከተለቻቸው፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። ለእናንተ የመዳንን መንገድ ይነግሩአችኋል!›› በማለት መጮህዋን ቀጠለች። ይህንን ደጋግማ ስለ አደረገች ጳውሎስ ተበሳጨ።

በመጨረሻም አንድ ቀን ሠራተኛይቱ መጮኽ በጀመረች ጊዜ ጳውሎስ ወደ እርስዋ ዘወር አለና በእርስዋ የነበረውን ጋኔን፣ ‹‹በኢየሱስ ስም ከእርስዋ ውጣ›› አለው፡፡ ወዲያውኑ ጋኔኑ ለቀቃት፡፡

በዚህ የባሪያዪቱ ጌቶች በጣም ተቈጡ! ያለ ጋኔኑ ባሪያዪቱ ልጅ ስለ ሰዎች መጪ ጊዜ መናገር እንደማትችል ዐወቁ። ይህም ማለት ለሰዎች የወደፊቱን ነገር ልትነግራቸው ስለማትችል ለጌቶችዋ ገንዘብ አይከፍሉም ማለት ነው።

ስለዚህ የባሪያዪቱ ጌቶች ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ሮማ ባለ ሥልጣናት ወሰዱአቸው፣ እነርሱም ደብድበው ወደ እስር ቤት ጣሉአቸው።

የሮማ ወታደሮችም ጳውሎስንና ሲላስን በእስር ቤት ውስጠኛ ክፍል አሰሩአቸው፤ እግሮቻቸውንም ከግንድ ጋር አሰሩአቸው፡፡ ሆኖም ግን እኩለ ሌሊት ላይ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘመሩ፡፡

በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ! የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ ወለል ብለው ተከፈቱ፣ የእስረኞቹ ሁሉ ሰንሰለቶችም ረገፉ።

የእስር ቤቱ ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቃ፣ የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ መከፈታቸውን ባየ ጊዜ በጣም ደነገጠ! እስረኞቹ ሁሉ ያመለጡ መሰለው፣ ስለዚህ ራሱን ለመግደል ዐሰበ። (እስረኞቹ እንዲያመልጡ ካደረገ የሮማ ባለ ሥልጣናት እንደሚገድሉት ያውቅ ነበር።) ነገር ግን ጳውሎስ ዐየውና፣ ‹‹ተው! ራስህን አትጕዳ። እኛ ሁላችንም እዚህ አለን›› ብሎ ጮኸ።

የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ ጳውሎስና ሲላስ እየተንቀጠቀጠ መጣና፣ ‹‹እድን ዘንድ ምን ላድርግ?›› ብሎ ጠየቀ። ጳውሎስ፣ ‹‹በጌታ በኢየሱስ እመን፣ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ›› ብሎ መለሰለት። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው። ጳውሎስ በቤቱ ለነበሩት ሁሉ ስለ ኢየሱስ የምሥራች ሰበከላቸው።

የእስር ቤት ጠባቂውና መላው ቤተ ሰቡ በኢየሱስ አምነው ተጠመቁ። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ለጳውሎስና ለሲላስ ምግብ አቀረበላቸውና በአንድነት ደስ አላቸው።

በማግስቱ የከተማው መሪዎች ጳውሎስንና ሲላስን ከእስር ቤት ፈቱአቸውና ከፊልጵስዩስ እንዲሄዱ ጠየቁአቸው፡፡ ጳውሎስና ሲላስ ልድያንና አንዳንድ ሌሎች ወዳጆችን ጐበኙና ከተማይቱን ለቀው ሄዱ፡፡ የኢየሱስ የምሥራች ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ ቤተ ክርስቲያንም ማደግዋን ቀጠለች፡፡

ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኢየሱስ የምሥራች እየሰበኩና እያስተማሩ ወደ ብዙ ከተሞች ተጓዙ። ደግሞም በአብያተ ክርስቲያናቱ ላሉ አማኞች ሊያበረታቱአቸውና ሊያስተምሩአቸው ብዙ መልእክቶችን ጻፉላቸው። ከእነዚህ መልእክቶች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ሆኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 16፡11-40።